መነሻ ገጽ

February 24, 2021EthiopianReporter.com

የሙያ ማኅበራት በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት መሳተፍ አለባቸው ተባለ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒትር ዴኤታ አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) ከሙያ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ይታያሉ

24 February 2021

ኤልያስ ተገኝ

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የሙያ ማኅበራት በከፍተኛ ትምህርት፣ የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ፣ ክለሳና ግምገማ፣ እንዲሁም ሙያን አክብሮ የሚሠራ ዜጋ በማፍራት እንቅስቃሴ ላይ ድርሻቸው የላቀ በመሆኑ፣ ከሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር ተሳስረው መሥራት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ‹‹የሙያ ማኅበራት ሚና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት›› በሚል መርህ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ከሙያ ማኅበራት ኃላፊዎችና ተወካዮቻቸው ጋር የምክክር መድረክ ባዘጋጀበት ወቅት ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ  አፈወርቅ ካሱ (ፕሮፌሰር) እንዳስታወቁት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ጥራት የሚለካው በግብዓት፣ በሒደትና በውጤት ላይ ነው ‹‹ያለንበት ዘመን የቴክኖሎጂ ዘመን እንደ መሆኑ መጠን ወቅቱን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የሙያ ማኅበራትና የባለድርሻ አካላት ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ ውስጥ የጥራት መለኪያ የሆኑትን የተማሪ ጥራት፣ የመምህራን ጥራት፣ እንዲሁም የሥርዓተ ትምህርት ጥራት ወሳኝ ስለሆኑ ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር ደግሞ ትልቅ ሚና ካላቸው አካላት መካከል የሙያ ማኅበራት ዋነኞቹ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው መስካቸውን ከለዩ በኋላ ሙያቸውን አክብረውና ራሳቸውን ለዚያ መስክ አስገዝተው እንዲገነቡ ከማድረግ አንፃር  ሥርዓተ ትምህርት ሲዘጋጅ የሙያ ማኅበራት ልዩ ድርሻ ይኖራቸዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ገበያውና ሙያው የሚፈልገውንና ገበያ ውስጥ ሊታይ የሚገባውን ባለሙያ እንዲታይ አድርጎ ከመቅረፅ አኳያ የሙያ ማኅበራት ከፍ ያለ ኃላፊነት  እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

አፈወርቅ (ፕሮፌሰር) እንዳስታወቁት፣ ጥናትና ምርምር አካባቢ የሚደረጉ ምርምሮች የአገር ዕድገትና ልማት የሚያግዙ፣ ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ ከማስቻልና በሙያቸው ቃኝተው ሙያዊ የሆነ አስተያየት እንዲሰጡ ከማድረግ አንፃር የማኅበራቱ ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ተግባር ይግዛው (ዶ/ር) ባቀረቡት የመነሻ ጽሑፍ፣ ከተለያዩ አካላት ማለትም ከሳይንስና  ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብና ጥራት ኤጀንሲ የሕክምና ትምህርትን በተመለከተ ምክር ለመስጠት፣ ስታንዳርድ ላይ የበኩሉን ለማበርከት ቋሚ ኮሚቴዎችን እንዳቋቋመ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ‹‹በአሁኑ ወቅት የጤና ትምህርቱ ምን ዓይነት ክፍተት አለበት? ምንስ መምሰል አለበት?›› የሚለው ላይ አማራጭ ምክረ ሐሳቦችን እንዳቀረበና ከዚህም በላይ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው፣ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሙያ ማኅበራት ጋር መሥራቱ ለማኅበራቱ በቂና ብቁ አባላትን ለማፍራት ጠቀሜታ ያለው መሆኑን፣ አገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ከሙያ ማኅበራት ጋር ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የሙያ ማኅበራቱም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ የሚሠሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች፣ 40 ሺሕ የሚጠጉ መምህራን፣ 212 የቅድመ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞች፣ 457 የትምህርት ፕሮግራሞች በማስተርስ ደረጃ፣ እንዲሁም  220 የፒኤችዲ ፕሮግራሞች እየተሰጡ እንደሚገኙ የሳይንስና  ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡