February 25, 2021 – Konjit Sitotaw
“ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ነዋሪዎቹ በደል እየተፈጸመባቸው ያለው በራሳቸው ልጆች መሆኑን፤ይህ ደግሞ ስቃያቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገባቸው ነግረውናል”
“የሴራ ፖለቲካ ዋና መለያው የሆነው የህወሓት ጁንታ ቀድሞ ኮንደም አደለ፤ በመቀጠል ወንጀለኞችን ከየቦታው ፈትቶ ለቀቀ፤ ከዛም የወንጀል ድምፆች በክልሉ የእለት ተእለት ዜና ሆኑ”
የሰሜን ምእራብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ብርሃን ሀይለ
ጁንታው የህግ ታራሚዎችን በመልቀቅ በትግራይ ከፍተኛ ዝርፊያ እንዲፈጸም አድርጓል፤ ሽንፈቱ አይቀሬ ሲሆንም “የሻቢያ ወታደር ሊደፍራችሁ ይመጣል” በሚል ሴቶችን ሰብስቦ ኮንዶም እስከማደል የደረሰ ፕሮፖጋንዳ መስራቱን የሰሜን ምእራብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ብርሃን ሀይለ አስታወቁ።

አስተዳዳሪው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የህወሓት ጁንታ ከ10 ሺህ በላይ የህግ ታራሚዎችን በመልቀቅ በትግራይ ክልል ከፍተኛ ዝርፊያ እንዲፈጸም አድርጓል፤ ሽንፈቱ አይቀሬ ሲሆንም የሻቢያ ወታዳር ሊደፍራችሁ ይመጣል በሚል ሴቶችን ሰብስቦ ኮንዶም እስከማደል የደረሰ ፕሮፖጋንዳ መስራቱን የሰሜን ምእራብ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ብርሃን ሀይለ አስታወቁ።
አስተዳዳሪው እንደተናገሩት፤ ጁንታው የመውደቁ ሁኔታ አይቀሪ መሆኑን በተገነዘበበት ወቅት ከ10ሺ የሚበልጡ የህግ ታራሚዎችን ከማረሚያ ቤት ፈትቶ ከተሞች ውስጥ በመልቀቅ በክልሉ ላይ ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን ከፍተኛ ዝርፊያ እንዲፈጸም በማድረግ በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍ ያለ ወንጀል ፈጽሟል።
በተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ፈጽመው በህግ ጥላ ስር የነበሩ ወንጀለኞችን ሳይቀር ፈትቶ መልቀቁን ያመለከቱት አቶ ሙሉ ብርሃን፣ በዚህ ተግባሩ በትግራይ ህዝብ ላይ ታሪክ የማይረሳው በደል መፈጸሙን አስታውቀዋል።
ዛሬ ይህንን ወንጀሉን ለመሸፈን እና ከደሙ ንጹህ ነኝ ለማለት ከሀገር ውጪ ባሉ ደጋፊዎች በኩል በአሳፋሪ የስም ማጥፋት ዘመቻ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
እርሳቸው በሚያስተዳድሩት አካባቢ ህብረተሰቡን በስፋት ማወያየት ተችሏል ያሉት አስተዳዳሪው፤ በዚህ ውይይት ህብረተሰቡ የገለጸው ጁንታው በህግ ማስከበር ዘመቻው ሙሉ በሙሉ ተሸንፎ ከመውጣቱ በፊት ሴቶችን በመሰብሰብ ሻቢያ ስለሚደፍራችሁ በሚል ኮንዶም ማደሉን ነው።
የሴራ ፖለቲካ ዋና መለያው የሆነው የህወሓት ጁንታ ቀድሞ ኮንደም አደለ፤ በመቀጠል ወንጀለኞችን ከየቦታው ፈትቶ ለቀቀ፤ ከዛም የወንጀል ድምፆች በክልሉ የእለት ተእለት ዜና ሆኑ ሲሉ ነው አቶ ሙሉብረሃን የገለጹት።
በአካባቢው በአስገድዶ መድፈር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊቱንና የኤርትራን ጦር ዩኒፍርም አድርገው መገኘታቸውንም አስተዳደሪው ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሙሉብርሃን ገለጻ፣ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊት የመከላከያ ሰራዊቱን ዩኒፎርሞችን በስፋት ለጥፋት ሃይሎቹ አሰፍቶ በማከፋፈል በሰራዊቱ ስም በትግራይ ህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል እንዲሰራ አድርጓል፤ በተመሳሳይ መልኩ የኤርትራ ወታደሮችን ዩኒፎርም በማልበስ ተመሳሳይ ወንጀል ፈጽሟል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ነዋሪዎቹ በደል እየተፈጸመባቸው ያለው በራሳቸው ልጆች መሆኑን መናገራቸውን አመልክተው ፣ ይህ ደግሞ ስቃያቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው መናገራቸውን ጠቁመዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍ ባለ ዲስፒሊን የሚገዛና የሚመራ መሆኑን ያመለከቱት አስተዳዳሪው ፣ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው የጁንታው ደጋፊዎችና ቅጥረኞች የመከላከያው ስም ለማጠልሸት የጀመሩት ስም የማጥፋት ዘመቻ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ከጥቃቱ በፊት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቤተሰብ የሆነና ለረጅም ዓመታት አብሮ የኖረ ለ20 ዓመታት ሕይወቱን ሰጥቶ ሲጠብቀው የነበረ ከመሆኑ አንጻር በሰራዊቱ ላይ የተጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ለትግራይ ህዝብ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም ብለዋል ።
ሰራዊቱ አሁንም ቢሆን በገዛ ሕዝቡ ላይ የከፋ በደል ለማድረስ ቀን ከሌት የሚባዝነውን የጁንታውን ርዝራዥ አደብ በማስያዝ የትግራይ ህዝብን ወደቀድሞ ሰላሙና ወደ አዲስ የልማት ምእራፍ ለማሻገር በቅንነት እየተንቀሳቀሰ ነው፣ በዚህም ህዝባዊነቱን እያስመሰከረ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአላማ በህዝቡ ውስጥ የተበተኑ ወንጀሎችን በማደን በክልሉ የተንሰራፋውን ሥርዓት አልበኝነት አደብ ለማስያዝ የክልሉ የፖሊስ ሃይል መደራጀቱን የፍትህ ተቋማትም ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በሰሜን ትግራይ ዞን ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ጠቁመው ፣ይህ እውነታ በመላው ትግራይ በቅርቡ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል ። ለዚህም የህዝቡ ሰላም ፈላጊነት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም አመልክተዋል ።
–
