
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን አስመልክ መግለጫ ሰጥቷል፡፡የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ወደ መጋቢት 16 እንዲዘዋወር መወሰኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን አውጥቶ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም መካከል በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የእጩዎች ምዝገባ አንዱ ነው፡፡ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ከእጩዎች ምዝገባ በመቀጠል የሚከናወነው ሌላው ተግባር የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ነው።
ቦርዱ የምርጫ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠሙትን ችግሮች አመላክቷል፡፡ የምርጫ ክልል ቢሮዎች ዝግጅት መዘግየት እና አስፈጻሚዎች ሰልጥነው ከተሰማሩም በኋላ ቢሆን ቢሮዎች ዝግጁ ሆነው ባለመገኘታቸው የቢሮ መከፈት መዘግየቱ፣ በተወሰኑ ክልልሎች አስፈላጊው ቢሮዎች ተዘጋጅተው ባለማለቃቸው የእጩዎች ምዝገባ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጀመር አለመቻሉ እና ለሁለት ዙር መከፈሉ ለምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የትራንስፖርት እጥረት እና የገለልተኛ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብሏል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልገው በመረዳት በመጀመሪያ ዙር የእጩዎች ምዝገባ በተጀመረባቸው ክልሎች ለ4 ቀናት ማራዘሙንም ገልጿል፡፡በሁለተኛ ዙር የእጩዎች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልሎችም ላይ የቢሮዎች ዝግጅት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ችግር ሆኖ እንደነበር መገንዘቡን ጠቁሟል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ተግባርንም ከ140 ሺህ በላይ እጩ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ ሆነው የሚሠሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነት ማጣራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጾ ይህም ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ እንደሚችል አመላክቷል።
ከክልሎች የሚገኘው የቢሮዎች ትብብር መዘግየቱ፣ የእጩዎች ምዝገባ ቀናት ከተጀመሩም በኋላ ዝግጁ ያልሆኑ የተወሰኑ ቢሮዎች የነበሩ በመሆኑ ፣ ፓለቲካ ፓርቲዎችም ተጨማሪ ቀናት በመጠየቃቸው እና የእጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ እንዲሁም በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠመው የቁሳቁስ ማጓጓዝ ችግር በመገምገም እና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ሥራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን የመራጮች ምዝገባን ከተያዘለት ቀን የካቲት 22/2013 ዓ.ም ወደ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም እንዲዘዋወር መወሰኑን ቦርዱ ገልጿል።
6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 እስከ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም ድረስ ይከናውናል ነው ያለው፡፡ ቦርዱ ለወደፊትም ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
