ግጭት በተካሄደበት የሰሜናዊ ኢትዮጵያዋ የትግራይ ክልል የቢቢሲ ዘጋቢ የሆነው ግርማይ ገብሩ በአገሪቱ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውሏል።
ለቢቢሲ የትግርኛ ቋንቋ አገልግሎት የሚሰራው ግርማይ ገብሩ የተያዘው በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ውስጥ በሚገኝ ካፍቴሪያ ውስጥ ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር ነው።
የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አምሰቱ ሰዎች የተያዙት ወታደራዊ የደንብ ልብስ በለበሱ ወታደሮች ሲሆን፤ በሁለት የወታደር ተሽከርካሪዎች በታጀበ መኪና መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ግርማይን ጨምሮ አምሰቱ ሰዎች ለምን ተይዘው እንደተወሰዱ ግልጽ አይደለም። ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት ሪፖርተሩ መቀለ ውስጥ ወደሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ተወስዷል።.
ህወሓትን ለማስወገድ በተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች የትግራይ ክልልን መቆጣጠራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ካስታወቁ በኋላ ካለፈው ኅዳር ጀምሮ ክልሉ በወታደራዊ ዕዝ ስር ይገኛል።
ወታደራዊ ግጭቱ የተባባሰው የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ነበር።
በውጊያው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል፤ በተጨማሪም በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችና የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ ነው።
ወደ ክልሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ለወራት እንዳይገቡ ከተከለከለ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ አገር ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ ገብተው እንዲዘግቡ ባለፈው ሳምንት ፈቅዷል።
የቢቢሲው ዘጋቢ የታሰረው ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) እና ለፋይናንሻል ታይምስ የሚሰሩ ሁለት ሌሎች ጋዜጠኞቹን የሚያግዙ ባለሙያዎች (ፊክሰር) መታሰራቸው ከተነገረ ከቀናት በኋላ ነው።
ሌላ ታምራት የማነ የተባለ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛም ባልታወቀ ምክንያት በወታደሮች ተይዟል።
የአምነስቲ ሪፖርት ባልተሟላ መረጃ የተዘጋጀ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ተቸ
ጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ ደረሰ የተባለው ጥቃት ምን ነበር?
የተባበሩት መንግሥታት የመብት ጥሰቶችን ለማጣራት ወደ ትግራይ ለመግባት ጠየቀ
በትግራይ የተከሰተው ግጭት አንኳር ነጥቦች ሲዳሰሱ
ባለፈው ሳምንት አንድ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ባለስልጣን “አሳሳች በሆኑ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ኤኤፍፒ እና ፋይናንሻል ታይምስ ወደ ትግራይ በመሄድ ዘገባ እንዲሰሩ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና በሠላም ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝተው ነበር።
“በፍጹም ብርሃኔ ላይ የቀረበ ይህ ነው የሚባል ክስ አልተነገረንም። ከመገናኛ ብዙሃን ጋር መተባበሩ ለመታሰሩ ምክንያት ሊሆን አይገባም፤ ስለዚህም በአስቸኳይ እንዲለቀቅ እንጠይቃለን” ሲሉ የኤኤፍፒ ግሎባል ኒውስ ዳይሬክተር ፊል ቼትዊንድ ባወጡት መግለጫ ጥሪ አቅርበዋል።
ፋይናንሻል ታይምስ ባወጣው አጭር መግለጫ የታሰሩትን ጋዜጠኞቹን የሚያግዙ ባለሙያዎች (ፊክሰር) ለማስለቀቅ “የሚቻለውን ሁሉ እርምጃ” እየወሰደ መሆኑን ገልጿል።
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የመንግሥት ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ድል መቀዳጀታቸውን ቢያውጁም በክልሉ ውስጥ ግጭቶች የቀጠሉ ሲሆን የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልተናሳም።
ቢቢሲ