May be an image of 1 person

ታላቁ ጥቁር አጤ ምኒልክ ገናነታቸው ከአውሮፓ አልፎ ታላቋ አሜሪካ ደርሶ ነበር፤ ከአድዋ ድል በኋላ የየስቴቱ ጋዜጦች የእሳቸውንና የእቴጌ ጣይቱን ፎቶግራፍ በፊት ገጻቸው ላይ እየለጠፉ ጽፈዋል።

የሉዚያና ግዢ መታሰቢያ ትርዒት ላይ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ በፕሬዚዳንት ቴዎድሮ ሩዝቬልት በተጻፈ ደብዳቤ እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር። የሉዝያና ግዥ መታሰቢያ ትርዒት አሜሪካኖች የሉዝያናን መሬት ከፋረንሳይ የገዙበትን መቶኛ ዓመት ለማክበር ያዘጋጁት ነው።

የንግድ ትርዒቱ ብዙ ነገር ያካተተ ነበር የሳይንሳና አዳዲስ ፈጠራዎች፣ የትምህርት፣ የስነ ጥበብ፣ የቴክኖሎጂ፣ የግብርና፣ የምግብ፣ የባህል፣ የኢንዱስትሪ ግኝቶች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ አንትሮፖሎጂ ዘርፎችን አካቷል።

ዳግማዊ ምኒልክ እንዲገኙ የተጋበዙት እዚህ ትርዒት ላይ ነበር። በቆንሲል ስኪነር የተላከላቸው የግብዣ ጥሪ ሁለት አይነት ነበር አንዱ ንጉሠ ነገሥቱ በአካል ወደ አሜሪካ መጥተው በትርዒቱ ላይ እንደ አንድ የክብር እንግዳ እንዲገኙ ሲሆን፤ ሁለተኛው ሁለተኛው ደግሞ የሀገራቸውን የምርትና የንግድ ናሙናዎች በትርዒቱ ላይ በማቅረብ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ነበር።

የምኒልክ ወደ አሜሪካ መጋበዝ ዜናው ይፋ ከደረገበት ከኦክቶበር 1903 ጀምሮ ትኩረት ስቦ ቆይቷል። ቆንሲል ስኪነር የጥሪ ወረቀቱን ከኋይት ሀውስ ተቀብሎ ገና ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ላይ ሳለ ወሬው ከአሜሪካ አልፎ አውሮፓና ኢትዮጵያ ደርሶ ነበር። ይሄንን የሰሙት የአሜሪካ ጋዜጦች ምኒልክ “ምን አሉ” በማለት ወሬ በመቃረም ይጽፉ ጀመር።ይህ ሁኔታ ስለንጉሡ መምጣት ይበልጥ ጉጉት እያሳደረ መምጣቱ ግድ ሆነ።

በኦክቶበር 29 ቀን 1903 በኢንዲያናፖሊስ የወጣው የሴንቲኒል ጋዜጣ “ንጉሡ በጦር መርከብ መምጣት እንዳለባቸው ገለጹ” (King says he must be brought over a warship) እስከ ማለት ደረሰ። በሀተታውም ላይ “ንጉሥ ምኒልክ ከንግሥት ጣይቱ ጋር ሆነው የሴንት ሉዊስን ትርዒት ለመጎብኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። ሆኖም በጉዳዩ ላይ የሞወስኑት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት አቢሲኒያ ከሚደርሰው ኮሚሽነር ስኪነር ጋር ከተገናኙ በኋላ መክረውበት እንደሆነ ታውቋል” ይላል።

በኖቬምበር 4 ቀን 1903 የታተመው የሴንት ሉዊስ ሪፐብሊክ ጋዜጣ ደግሞ “የአቢሲኒያዋ ንግሥትም የዓለም ትርዒቱን ይጎበኙ ይሆናል” (Empress of Abyssinia may visit the world’s fair) የሚል ልብ ሰቃይ ርዕስ ይዞ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ በግንባር ገጹ ላይ አቅርቧል።

“ምኒልክ በ1904 ወደ አሜሪካ ለመምጣት ከወሰኑ ንግሥቲቱ እንደሚያጅቧቸው ተሰምቷል።” ካለ በኋላ “የዓለም ትርዒቱ ከአቢሲኒያው ዳግማዊ ምኒልክ በተጨማሪ ዝነኛዋን ንግሥት ጣይቱንም (Celebrated Empress Taitu) በነገሥታት ጉብኝት ሊያስመዘግብ ይችላል። ንጉሡ የሚመጡ ከሆነ ንግሥቲቱን ይዘዋቸው እንደሚመጡ የተሰማው ከዋሽንግተን ነው።

በትናንትናው ዕለት እዚህ የደረሱት የሴኔተር ኮክሬል ልጅ ታዋቂው አለን ኮክሬል ሲናገሩ ‘ምኒልክ ግብዣውን ተቀብለው ለጉብኝት ወደ አሜሪካ ይመጣሉ ብዬ አስባለሁ። ሶመጡ ንጉሣዊ የክብር አቀባበል ይደረግላቸዋል። የመንግሥት እንግዳም ናቸው’ ብለዋል።

ንጉሡና ንግሥቲቱ ከነተከታዮቻቸው በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከብ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ እንዲጓጓዙ ይደረጋል። ለመመለሻ ጉዞውም የጦር መርከብ ይቀርብላቸዋል። ሚስተር ኮክሬል እንዳሉት ‘ይህ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ መ/ቤት የተያዘ ነው።’ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ባለሥልጣናት በዓለም ትርዒቱ ስም ለሚስተር ኮክሬል እንዳረጋገጡላቸው ለንጉሠ ነገሥት ምኒልክ የጦር መርከብ ማቅረቡ ባስፈለገ ጊዜ በሜዲትራንያን ቀጠና ከሚገኘው የባህር ኃይል ስኳድሮን ይቀርብላቸዋል።

ብዙዎቹ የንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ፖሊሲዎችና ድሎች ምንጫቸው የንግሥት ጣይቱ አእምሮ ነው። እርሳቸው (ጣይቱ) የሚያስደንቅ ጠንካራ ስብዕና አላቸው። ቃላቸውም በአቢሲኒያ የመንግሥት ጉዳዮች ውስጥ ትልቅ ክብደትና ቦታ ያለው ነው።” ካለ በኋላ በመጨረሻ ከሮማ የተገኘውን ዜና እንዲህ ሲል ያስደግፋል።

“የአውሮፓ ተወላጅ የሆኑት የአቢሲኒያው የተከበሩ የምኒልክ አማካሪ ኢልግ በቅርቡ ለዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ኢጣልያ ነበሩ። እዚያም ሳሉ ለአሜሪካው የዓለም ንግድ ትርዒት ተጠሪ እንደገለጹት ንግሥቲቱ ከባለቤታቸው ጋር ኤክስፖውን ለመጎብኘት እያሰቡበት ይገኛል…ብለዋል።” ይላል።

ምኒልክ ለቀረበላቸው ጥሪ በሁለት መልክ ነበር ኦፊሴላዊ መልስ የሰጡት። ሀገራቸው በትርዒቱ እንድትሳተፍ ለቀረበላቸው ጥሪ የትርዒቱ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ለዴቪድ ሮውላንድ ፍራንሲስ ደብዳቤ ሲልኩ፤ በአካል ራሳቸው እንዲገኙ ከመንግሥት (ከሩዝቬልት) ለቀረበላቸው ግብዣም እንዲሁ ደብዳቤ ልከዋል። ለሩዝቬልትና ለትርዒቱ ፕሬዚዳንት የጻፏቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ስኪነር በአድራሻቸው ወስዶ አድርሷል።

ለትርዒቱ ፕሬዚዳንት የተጻፈው የምኒልክ ደብዳቤ በሴንት ሉዊስ ሪፐብሊክ ጋዜጣ ላይ በፌብሯሪ 25 ቀን 1904 ወጥቷል። ከዚያው ጋር ንጉሡ በሥራ ምክንያት በአካል መገኘት አለመቻላቸውን ስኪነር ግልጽ ማድረጉም ይፋ ሆኗል።

ጋዜጣው የምኒልክን የአማርኛ ደብዳቤ ስኪነር ካቀረበው የእንግሊዝኛ ትርጉም ጋር በማስደገፍ ትንታኔ ሰጥቶበታል።

የምኒልክ መልእክት እንዲህ የሚል ነበር..

“ሞዓ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ።

ይድረስ ከ…አክስፓዚሲዮን ፕሬዚዳንት

ሰላም ለእርስዎ ይሁን

በቆንሲል ጀኔራል ሮ. ስኪነር የላኩት ደብዳቤ ደረሰልኝ።

በኢትዮጵያ ስም የኤክስፖዚሲዮን ቦታ ለማቆየት ስላሰቡልኝ እጅግ ደስ አለኝ። ግን ጊዜው አጠረ እንጂ እኛም በሀገራችን ከሚገኘው እቃ አንድ አንድ አይነት እንዲሰበሰብ አዘናል። ይህ የጀመሩት ኤክስፖዚሲዮን በደህና እንዲፈጸምልዎ እግዚአብሔርን እንለምናለን።

ታህሣሥ 17 ቀን 1896 ዓ.ም አዲስ አበባ”

ጋዜጣው ቆንሲል ስኪነር በዝርዝር የተናገረውን ካቀረበ በኋላ “በመንግሥት ሥራ ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱ በአካል ሴንት ሉዊስ ተገኝተው እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ላለመቀበል ተገደዋል” ማለቱን ይፋ አድርጓል።

እንዲህም ሆኖ ግን የምኒልክን መምጣት በምስጢር ተይዟል በማለት አንዳንድ ጋዜጦች ያወጡ ነበር።

ኮሎምቢያ ኪዩሪየር (Colombia Courier) የተባለ በዋሽንግተን ስቴት ኪንዊክ ከተማ የሚታተም ጋዜጣ “ምኒልክ ሊመጡ ይችላሉ” ብሎ የምኒልክን ፎቶ አስደግፎ ባወጣው ጽሑፍ “የሰለሞን የልጅ ልጅ…የሴንት ሉዊስን ትርዒት ይጎበኙ ይሆናል። ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት በቀረበላቸው ልዩ ግብዣ መሠረት እንደሚጠበቀው የአቢሲኒያው ንጉሥ ምኒልክ ትርዒቱን የሚጎበኙ ከሆነ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን የስነጥበብና የሳይንስ ፈጠራን የሚመለከቱ እጅግ ስሜት ሰጪ ሰው ይሆናሉ…” ካለ በኋላ ምኒልክን ልዩ የሚያደርጋቸው ታሪካዊ ባህርያት እንደሚከተለው አቅርቧል…”ዳግማዊ ምኒልክ የአፍሪካ ኃይል ንጉሥ ናቸው።

የጭለማዋ አህጉር ሌሎች ሀገሮች መሪዎች በአውሮፓ ኃያልን ሥር ወድቀዋል። ግዛታቸውንም በቅኝ ተገዥነት ወይም ጥገኝነት ተይዘዋል። የነጮች ደምና ስልጣኔ የበላይነት ጉዳይ ሉዓላዎነቷን በአልበገር ባይነትና በነፃነት ማድከበሯ በአረጋገጠችው በአቢሲኒያ ላይ አይሠራም።

ላለፉት 16 ዓመታት በዙፋን ላይ የቆዩትና በቁርጠኝነት መተላለፊያውን ዘግተው ቆመው ከኬፕ (ሳውዝ አፍሪካ) እስከ ካይሮ የሚለውን የሲስል ሮድስን (በደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን) ህልም ያከሸፉ ምኒልክ ናቸው።

እንደ ስመ- ጥሩው ቅድመ አያታቸው እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ንጉሥ ዳዊት ምኒልክ በግዛታቸው ላይ የሚረማመዱን ግዙፎች ወጥተው ለመግጠም አይፈሩም። የነጭ ኃይሎች ጎልያድ ምንም ቢሆን የአቢሲኒያውን ንጉሥ መውረርም ሆነ ማስፈራራት አልተሳካለትም።” ይላል። ምንጭ…ታላቁ ጥቁር ኢትዮ- አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክንጉሤ አየለ ተካየአድዋ ድል ውጤት ማለት ይህ ነው።

#ክብር #ለእምዬ#ምኒልክ!!!

#ክብር#ለአድዋ#ጀግኖች!!!