March 5, 2021Konjit Sitotaw

May be an image of 1 person, sitting and suit

በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች በመገምገም የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው ኮሚቴ በግጭቱ ውስጥ የሱዳንና ግብጽ ድጋፍ እንደነበረበት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሀሙ ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው ይህንን የገለጹት ኮሚቴው ከትግራይ ክልል ውጭ በመተከልና በሌሎች አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን ተመልክቶ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

በሱዳን ድንበር ላይ ታጣቂዎችን በማሰልጠንና ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ንግዶች ሲከናወኑ እንደነበር ከሕብረተሰቡና ከመተከል ኮማንድ ፖስት መረዳታቸውን ነው በመግለጫቸው ያብራሩት፡፡

የተፈጠረው ግጭት የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ረዘም ያለ ዝግጅት የተደረገበት፤ በኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ ሌላ አጀንዳ የነበራቸው አካላት “ክልሉ ሊፈርስ ነው ልትወረሩ ነው፤ ታጠቁ፤ ተዘጋጁ፤” እያሉ ይቀሰቅሱ እንደነበር ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡

May be an image of 1 person, standing, wrist watch and indoor

በአብዛኛው ወረዳዎች የሸሹ ታጣቂዎች መመለሳቸውን፣ 3ሺሁ የሚሆኑ ታጣቂዎች ደግሞ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ እጃቸውን መስጠታቸውን እና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የተደረጉ መሆኑንም አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡ በመተከልና አካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ68 ሺህ በላይ የሚሆን የጉሙዝ ማኅበረሰብ ሸሸቶበት ከነበረው ጫካ እንደተመለሰም ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሚሊሻዎችን በመመልመልና በማሰልጠን የዝግጅት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ አብዱላሂ ጠቅሰዋል፡፡

የጥፋቱ አካል የነበሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን ከቦታቸው በማንሳት ለሕግ የማቅረብ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ከኮማንድ ፖስቱ መረዳታቸውን አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ከተለያዩ የአካባቢው የሕብረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ እንዳልሆነና ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት የፈጠሩት ግጭት መሆኑን መረዳታቸውን አቶ አብዱላሂ ገልጸዋል፡፡

May be an image of 1 person

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ እና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በተጠለሉበት የተለያዩ ቦታዎች የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ነው ሰብሳቢው የተናገሩት ፡፡

የሰብዓዊ ድጋፉ ባልተቆራረጠ መልኩ እንዲከናወን የፌደራልና የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ-አመራር ኮሚሽ ጋር በጋራ የሚሰራ የቴክኒክ ኮሚቴ ቡድን በማዋቀር እየተሰራ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ከፍ ከማለቱ የተነሳ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ የማይደርስበት ሁኔታ መኖሩንም ሰብሳቢው መግለጻቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 125 ሺህ እንደሆነ ነው አቶ አብዱላሂ በመግለጫቸው ያነሱ ሲሆን በቂ የሰብአዊ ድጋፉ ለተፈናቃዮች እንዲደርስ መንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አቶ አብዱላሂ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቦታቸው የመመለስ፣ የስነ-ልቦና ግንባታ ስራዎችን መስራትና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

(ኢ ፕ ድ)