March 7, 202

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ ለመወሰን ለሁለተኛ ጊዜ ያደረገው ሙከራ ያለስምምነት ተበተነ። ምክር ቤቱ በአየርላንድ አቅራቢነት በትግራይ ክልል ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ መግባትን በሚጠይቀው ረቂቅ ላይ ህንድ ፣ ሩስያ እና በተለይም ቻይና በድጋሚ ተቃውመውታል።

ትናንት ዓርብ ምሽት ያለውጤት የተቋጨው የምክር ቤቱ ስብሰባ ከስምምነት ተደርሶ ቢሆን በኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ መግለጫ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ያወጣ እንደነበር የሶስቱ ሀገራት ዲፕሎማቶች አስታውቀዋል። በአየርላንድ የቀረበው መግለጫ ጣልቃ ገብነት አልያም ማዕቀብ እንዲጣል መጠየቅ በውል የለየ አልነበረም ሲል የአሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። ነገር ግን በትግራይ ክልል የሰፈነው አመጽ እና ግጭት እንዲያበቃ ጥሪ መቅረቡን ገልጿል።

ቻይና አመጽ እና ግጭትን ማስቆም በሚል በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ አይገባም ብላለች ። የሰብአዊ ድጋፎችን ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ለምክር ቤቱ ማሳወቋን እንዲሁም ህንድ በኋላ ላይም ሩስያ የቻይናን ሃሳብ መደገፋቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ዲፕሎማቶች ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።