ሙሉአለም ገ.መድህን

ደንቢያ ጣናን ተንተርሳ ሜዳማ ተፈጥሮ አላት። ታሪከ ብዙ ነች። በወርቃማው የጎንደር ዘመን የመንግስት ድርሻ ነበራት፤ የዓለም ሰገድ ፋሲለደስ አባት የነገሱት ደንቢያ ነበር። የደጃች ማሩ ባድማ_ማሩ ቀመስ ደምቢያ!!

ሩቅ ዓላሚው ንጉሣችን ቴዎድሮስ ፊደል የቆጠረባት፣ ራዕዮን የወጠነባት፣ ዘመነ መሳፍንትን ለመገርሰስ በተደረገው ትግል የዘመነ መሳፍንት የመጀመሪያ አከርካሪ የተሰበረው ደንቢያ ጉራምባ_ሚካኤል በነበረው የነ ራስ አሊ የጦር ሰፈር ነበር። እነ ደጃች ጎሹ ፣ እነ ደጃች ወንድ ይራድ የተሸነፉትና የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጥንስስ የተጠነሰሰባት ቦታ ነች_ደንቢያ።

[ኤርትራውያን] ሐማሴኖቹ ምንጫችን ነች ይሏታል። ተስፋፊው ኦነጋዊ ኃይል ‘ደምቢያ የሚባል ጎሳ ነበረን’ (እና ዛሬ ቀልጦ ቀረ🙈) እያለ ተረክ ሊፈጥርባት ታትሯል። አህመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ አህመድ) መቀመጫውና መውደቂያው አድርጓታል። ገላውዲዮስ የጠማውን ድል አስመዝግቦባታል። ብቻ ምን አለፋችሁ ደምቢያ በኢትዮጵያ የታሪክ ገጽ ምኩራብ ሆነው ታሪክ ስጋና ደም ለብሶ ከሚነበብባቸው ጥንታዊ ቦታዎች አንዷ ነች!!

መሬቱ ለም ነው። ቆላማውን የመዘጋ መሬታችን ያስንቃል! ከጥራጥሬ እስከ ቅባት፣ ከአትክልት እስከ ፍራፍሬ፣ ከቅመማቅመም እስከ በርበሬ፣… ድረስ ሁሉንም ታመርታለች፤ በሰቀልት ጤፍ የተሰረገ ሰርግ ትዳሩ ይጸናል ይሉታል። (በእንጀራው ንጣትና ልምላሜ ታዳሚው ፍስሃ ወርዶለት ጥንዶች ላይ ምርቃት ስለሚያዘንብ ነው ትዳራቸው የሚጸና ተብሎለታል) የድልብ ሰንጋው በል የወተት ላሙ ሰርክ አይነጥፍባትም_ደምቢያ!

ችግሩ ያለው የደምቢያን ጸጋ ወደ ገበያ ዕድል ለመቀየር የሚያስችል የመንገድ ትስስር ያልነበረ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል። ያው በራስ ጸጋ ልክ ያለመልማት የአደህይቶ መግዛት አንዱ ፖሊሲ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል።

ዛሬም ከሻውራ_ደልጊ_ቆላድባ መንገድ የጠጠር መንገድ ነው። የአካባቢው መሬት ዋልካ በመሆኑ ሰኔ ግም ሲል የጠጠር መንገዱን ተሽከርካሪ አይደፍረውም፤ ይህ በመሆኑ ሰፊ የገበያ ዕድል ያለበትን አካባቢ በጸጋው ልክ የገበያ ዕድል እንዳይኖረው አድርጎታል።

የመንገድ ልማት በባህሪው ኢኮኖሚን ለማሳለጥ፣ የህዝብ መስተጋብርን (ማህበራዊ ግንኙነትን) ከፍ ለማድረግ ሁነኛ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም በክልሎች ለታየው ያልተመጣጠነ ዕድገትም ሆነ አስተዳደራዊ ተደራሽነት በመንገድ ዘርፍ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታ ራሱን የቻለ ጉልህ ተጽዕኖ ነበረው፡፡ እናም ይህ የቀደመ ያልተመጣጠነ ዕድገት ምንጭ የሆነ የተዛነፈ አሰራር ሊታረም ይገባል። የ

2014 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መስሪያ ቤት በአማራ ክልል ውስጥ ሊሰራቸው ከሚገቡ የመንገድ ልማት ዕቅዶች ውስጥ የቅድሚያ ባጀት ሻውራ➡️ ደልጊ➡️ ቆላድባ (ከመናገሻ ጎንደር_ጎርጎራ ዋናው መንገድ) ጋር ማገናኘት ሊሆን ይገባል። ይህ ከሰማንያ ኪሎ ሜትር የማይበልጥ የመንገድ ፕሮጀክት በባጀት ጉድለት ለማጠፍ እንኳ ያስቸግራል፤ የልግመት ካልሆነ በስተቀር! 2014 የማይታጠፍ ቀጠሮ ይዘናል!

አገኘሁ ተሻገር-Agegnehu TeshagerEthiopian Roads Authority

~

ወደዛሬው የብስራት ዜና ስንመለስ፦ በጎርጎራ ‹የገበታ ለሀገር› የልማት ውጥን ከሚለማው ፕሮጀክት ውጭ 134 የሚደርሱ ባለሃብቶች የቦታ ጥያቄ አቅርበዋል፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሰሳቸውን ቀድመው የጨረሱ (በርካቶች ናቸው) በዛሬው ዕለት የቦታ ርክክብ ያደርጋሉ።

እያንዳንዳቸው እስከ 500 ሚሊዮን ብር የሚደርሱ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ መዝናኛ ሎጂዎች፣ በግብርና እና ማዕድን ልማት ለመሳተፍ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ጥናት አቅርበዋል። መንገድ ብርቁ ሆኖበት ለኖረው ሕዝባችን በጎርጎራ የተጀመረው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የልማት ትንሳዔው ምልክት ነው።

እያደገ በመጣ የሕዝብ ፍላጎት ውስጥ ለልማት የሚኖር መረዳት የኀልውና ያህል ቦታ ተሰጥቶታል። በአጭሩ ያለ ልማት የማይተነፍስ ሕዝብ ተፈጥሯል። የሠላም ዋጋው የትድረስ እንደሆነ ጎርጎራ ህያው ምስክር ነች። በአንድ እጃችን የተከዜ ሸለቆ ሽፍቶችን እየቀጣን በሌላኛው እጃችን ትርጉም ያላቸው የልማት ስራዎችን እናስተባብራለን። እንደእውነቱ ከሆነ የጎርጎራ የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች ሙሽርነት የተፈጥሮ በረከቷና የሠላም ይዞታዋ እንጅ፣ የቀድሞ ወዳጆቻችን መላልሰው ሲገልጹት እንደከረሙት “የጎጥ ቅሬታ የፈጠረው የደም ካሳ ውጤት” አይደለም። አካባቢው ልማት የማይወድለት ብረት አንጋች ሆኖ እንዲቀር ዛሬም ያልነጠፈ ምኞት ያላቸው “ወንድሞቻችን” ከቀቢፀ ተስፋ እንዲወጡ በድጋሚ በአደባባይ ልመክራቸው እወዳለሁ!

በዘመናዊው ዓለም የአንዱ ልማት ለሌላው የገበያ ዕድል ነው! ይህን መርህ መቃረን የጤና አይደለም። ዘላለማዊ አብሮነትን የሚሻ ሕዝብ ይዘን ጥላቻን አንስበክ፤ ምቀኝነትን አናውርስ! አጀንዳዎቻችን የሕዝባችንን ህልውና፣ ኑሮና ህይወት በዘላቂነት በመለወጥ ላይ ያተኮሩ ይሁኑ። የፖሊስ ሃሳብ ማፍለቅ የማችሉ ጭንቅላቶች ጥላቻን ሲረጩ እንዲውሉ አንፍቀድላቸው።

~

በተረፈ ጎርጎራ የልማት ትንሳዔዋን ተከትሎ ደምቢያ መስኩ ብቻ ሳይሆን የጣና ዙሪያ ወረዳዎች የመሬት አስተዳደራቸው በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል። የመሬት ባንክ ውስጥ ያልገቡ መሬቶች በፍጥነት ሊካተቱ ይገባል። የመሬት ኦዲት ሥርዓቱ ለሙስና በር የሚዘጋ ካልሆነ ወደተለመደው ሥርዓታዊ ንቅዘት ይከታል። ከመሬት ካሳ ጋር ተያይዞ ያለው በደለኛ አሰራር ሊታረም ይገባል። አርሶ አደራችንን የ15 ዓመት የሰብል ምርቱን ግምት አስልቶ ከማሰናበት የከረመ ግፍ ተላቆ አርሶ አደሩ ከነ ልጆቹ በአካባቢው ልማት የጋራ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል። በተለየ ሁኔታ በቤቶች ልማት (Real State) ዘርፍ የሚሳተፉ አካላት ከካሳ ክፍያ ባሻገር አርሶ አደሩ (መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችም ታይተው) ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው የሚያስችል አስገዳጅ ውል እንዲገቡ ማድረግ ይገባል።

በጎርጎራ ሰማንያ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኙ ከተሞችና ወረዳዎች ሁሉ የልማት ትንሳዔው ተካፋዮች በመሆናቸው በፍጥነት ዘመናዊ አስተዳደርና ስልጡን አሰራር እንዲከተሉ ማድረግ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ የአራቱም ዞኖች (ማዕከላዊ፣ ደቡብ፣ ምዕራብና መናገሻ ጎንደር [የልዩ ዞኑ]) አመራሮች በሰማኒያ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ስር ያሉ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ላይ የጎርጎራ ልማት ትንሳዔን ታሳቢ ያደረገ የአደረጃጀትና አስተዳደራዊ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባችኋል። በዚህ ረገድ የጎንደር እና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም መጠቀም ይመከራል።

~

እነ ዲያስፖራ Smart Village Project ወጥናችሁ መናገሻዋን ከጎርጎራ ጋር አዋህዱ! ለፋኖ ወንድሞቻችን ጥይት ሳይሆን ትራክተር የመግዛት ባህል አሀዱ ብላችሁ ጀምሩ። እያረሰ ዳርድንበሩን ያስከብራል። የገቢ አቅሙ ሲያድግ የሠላም ዘብነቱ እጥፍ ይጨምራል። እናተም ኢንቨስትመንትን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ማረፊያችሁን ታልማላችሁ። እስራኤል፣ ቻይና፣ ሕንድ፣…የመሳሰሉ ሀገራት በዲያስፖራ ትክሻ ነው እዚህ ደረጃ የደረሱት፤ የራሳችሁ ህልም ቢኖርም ተሞክሮ መጋራት አይከፋም!

***

ጉዛራ ጎርጎራ ጎንደር እና መሰል እውነተኛ ተቆርቋሪዎች የልማት ቁጭታችሁና ውትወታችሁ ስለሰመረ እንኳን ደስ አላችሁ። (እዚህ ያልተጻፉ ቀጣይ ተግባራት ስላሉን በጋራ እንመክራለን)