በመተከል ዞን የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ለአምስት ዓመታት ዝግጅት የተደረገበት ነው ተባለ

7 march 2021

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የወሰዱ ግለሰቦች የጉሙዝ ወጣቶችን በማሠልጠን ለዕኩይ ተልዕኮ ማዘጋጀታቸው ተጠቁሟል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ለአምስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረገብት መቆየቱን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲከታተል የተቋቋመው ኮሚቴ ገለጸ።

በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ እንደገለጸው፣

በመተከል ዞን ከሦስት ሺሕ በላይ ታጣቂዎችና በእነሱ አማካይነት ጫካ ገብተው የነበሩ ከ68 ሺሕ በላይ የጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል፡፡

ኮሚቴው ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ሲሆን፣ በዞኑ ያለውን ሁኔታ መጎብኘቱን አስረድቷል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አብዱላሂ ሀሙ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ኮሚቴው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

በዞኑ ተከስቶ በነበረው ግጭትም የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ሰብዓዊ ቀውስ ማጋጠሙንና ንብረት መውደሙን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ዘርፈ ብዙና ባለፉት አምስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ መሆኑን መገንዘቡንም  ገልጸዋል።

“በዞኑ በኢንቨስትመንት ስም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የወሰዱ ግለሰቦች የጉሙዝ ወጣቶችን በማሠልጠን ለእኩይ ተልዕኮ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል፤” በማለት ነው የተናገሩት።

በዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም እያሰፈነ መሆኑን ኮሚቴው መታዘቡን ገልጸዋል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ወደ ጫካ ገብተው ሸፍተው የነበሩ የጉሙዝ ታጣቂዎችም መንግሥት ያደረገውን የማግባባትና የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም እየተመለሱ መሆኑን አቶ አብዱላሂ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ታጣቂዎችና በታጣቂዎቹ አነሳሽነት ወደ ጫካ ገብተው የነበሩ 68 ሺሕ ገደማ የጉሙዝ ማኅበረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መግባታቸውን ኮሚቴው ማረጋገጡን ገልጸዋል።

ሪፖርተር