7 ሰአት በፊት

አቶ ዳውድ ኢብሳ

የፎቶው ባለመብት,

GETTY IMAGES

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከጥቂት ወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ እንደማይሳተፍ ባወጣው መግለጫ አሳወቀ።

በሌላ በኩል በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ሌላኛው የግንባሩ ቡድን ግን በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ቢገልፅም ዕጩ ስለማስመዝገቡ ግን ምንም ያለው ነገር የለም።

በአቶ ዳውድ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችሉት አመቺ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን ገልጾ፤ በገዢው የብልጽግና ፓርቲ ዘንድ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊ መስፈርቶች ለማሟላት ፍላጎት አለመኖሩ ከምርጫው ለመውጣቱ ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 2013 .ም የሚካሄድ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ደግሞ ሰኔ 5 2013 .ም እንደሚካሄድ የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ያስረዳል።

በዚህ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳሉ።

በበርካታ የአገሪቱ ክፍል ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን የዕጩዎች ምዝገባ በተራዘመባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የካቲት 30/2013 .ም ያበቃል።

ኦነግ በምርጫው ውስጥ እንደማይሳተፍ ባመለከተበት መግለጫው ላይ ለአገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተግባራዊ ቢደረጉ ይጠቅማሉ ያላቸውን እርምጃዎችን ጠቅሷል።

የምርጫ 2013 ተስፋ እና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተገፍቶ መውጣቱንገለፀ

ምርጫ 2013 እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተጣለባቸው አምስቱ የቦርድ አባላት

በዚህም መሠረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉም የፓለቲካ እስረኞችን እንዲለቀቁ፣ የተዘጉና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጽ/ቤቶች እንዲከፈቱ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ሁሉም ጦርነቶች በማቆም ሁሉን ያካተተ ድርድር እንዲደረግ፣ የአገሪቱ ቁልፍ ተቋማት ገለልተኛና ከአድልዎ የፀዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት የፓለቲካ ውይይት ሂደት እንዲጀመር ጠይቋል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ በመግለጫው በምርጫው እንደማይሳተፍ ይግለጽ እንጂ፤ ሌላኛው በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የግንባሩ አካል ግን በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ለቢቢሲ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ጥር በኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ግንባሩ በሁለት ወገን በመሆን የተለያዩ አቋሞችን እያንጸባረቀ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም የረጅም ጊዜ የድርጅቱ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ በአንድ ወገን ሆነው ድርጅቱን እየመሩ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ደግሞ በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመሩ ሌሎች የግንባሩ አመራር አባላት በግንባሩ ስም እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።

ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ አስገብተው የነበረ ሲሆን፣ ቦርዱም በግንባሩ ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባትና ልዩነት ሁለቱም ወገኖች በሕገ ደንባቸው መሠረት ተነጋግረው እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

አቶ አራርሶ ቢቂላ እና አቶ ዳውድ ኢብሳ

የፎቶው ባለመብት,

ONN/GETTአቶ አራርሶ ቢቂላ እና አቶ ዳውድ ኢብሳ

በአቶ አራርሶ የሚመራው የኦነግ አመራር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ቀጀላ መርዳሳ እንዳሉት ግንባሩ ከምርጫው መውጣትን በተመለከተ ውሳኔ ላይ አልደረሰም።

ሊቀ መንበሩ ማለት ድርጅቱ ማለት አይደለምያሉት አቶ ቀጀላ፣ ድርጅታቸው የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩበትም በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ እንቅፋት የሆነብን የውስጣችን ችግር ነው። የፓርቲው ሊቀ መንበር የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ አይደለምበማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ግንባሩ አሁን ባለበት ሁኔታ እንዴት በምርጫው እንደሚሳተፍ አቶ ቀጀላ ሲገልጹ የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን አዲስ አመራር ለመምረጥ እየሰራን ነውበማለት ሊቀ መንበሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ ግፊት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኦነግ ባወጣው መግለጫ ላይ ግንባሩ ተዘግተውብኛል ያላቸውን ጽህፈት ቤቶቻቸውን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ቀጀላ አዲስ አበባ የሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር እጅ ስር መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ውጪ በተለያዩ ቦታዎች ያሉት የግንባሩ ጽህፈት ቤቶች የተዘጉት በአቅም ማጣት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸውና አለ ባሉት የአስተዳደር ችግር ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግር የለም ማለት አይደለም ነገር አብዛኞቹ የራሳችን የውስጥ ችግሮች ናቸው። እኛ የፈጠርናቸው የውስጥ ችግሮችና አመራሮች ተገቢውን አመራር ባለመስጠቱ ነውበማለት ከምርጫው ተገፍተን ነው የወጣነው የሚለውን ሃሳብ አይቀበሉትም።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍላጎቱ ውጪ በደረሱበት ጫናዎች ለመውጣት መገደዱን ማስታወቁ ይታወሳል።

ኦፌኮ ይህን ውሳኔውን ያሳወቀው በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚገኙት ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋትና የአመራርና የአባላቱ መታሰርን እንደምክንያት በማስቀመጥ ከመጪው ምርጫ ተገፍቼ ወጥቻለሁ በማለት ነው።

ከምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን የገለጹ ፓርቲዎችን በተመለከተ በሚቀርቡ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ ከቀናት በፊት የገዢው የብልጽግና ፓርቲ የዓለም አቀፍና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳን (/) ጠይቆ ነበር።

ቢቂላ (/) እንደሚሉት በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሳተፍ ታግሎ ከማሻሻል ይልቅ፣ በትንሹም በትልቁም ምክንያት ከምርጫ መውጣት ሕዝቡ የፖሊሲ አማራጭ እንዳያገኝ የሚያደርግ ውሳኔ ነው ብለዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላትና ጽህፈት ቤቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተም እነዚህን የቀረቡ ስሞታዎች በዝርዝር ቀርበው ማጣራት ተደርጎ አብዛኞቹ ክሶች መሰረተ ቢስ ሆነው ተገኝተዋልሲሉ ተናግረዋል።

ችግሮች አያጋጥሙም ማለት እንደማይቻል የገለጹት ቢቂላ (/)፤ እነዚህንም ለማረምና ለማስተካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የአስተዳደር መዋቅሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ቢቢሲ