March 11, 2021 – Konjit Sitotaw
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ቆይታ ከቪኦኤ ጋር ፦

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ከሰሞኑ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅሩን መዘርጋት የቻለው 72 በመቶ ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል።
ትግራይ ኮማንድ ፖስት ስር ነው የምትገኘው ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የመደራጀት ስራ እየሰራ ቢሆንም በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ ችግር አለ ብለዋል።
ችግሩንም ሲያብራሩ፥ በአዋጁ መሰረት መላውን ትግራይ ከምዕራብ ትግራይ እስከ ደቡብ ትግራይ መቆጣጠር ያለበት የሀገር መከላከያ ኃይል ነው ነገር ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ መዋቅሩን መዘርጋት አልቻለም።
በምዕራብ ትግራይ ግዚያዊ አስተዳደሩ አልገባም፤ በደቡብ ትግራይ የተወሰኑ ወረዳዎች (አላማጣ እና ኮረም) አልገባም ይህ ያሆነው ቦታዎቹ በአማራ ልዩ ኃይል እና በአማራ ሚሊሻ በመያዛቸው ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሙሉ በአዋጁ መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህጋዊ ሰውነት ያለው በመሆኑ በሁሉም ቦታ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የመምስረት ስልጣን ቢሰጠውም በተጠቀሱት ቦታዎች እስካሁን አልገባም በዚህ ምክንያት ነው 72% ተብሎ የተገለፀው ሲሉ አስረድተዋል።
አብዛኛው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተዋቅሮ ስራ ጀምሯል ነገር በማዕከላዊ ትግራይ አንዳድን ቦታ በፀጥታ ችግር ስራ እንዳለጀመረ ጠቁመዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በደቡብ አላማጣ እና ኮረም፣ በምዕራብ ዞን በአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ መስተዳደሩ ትክክል እንዳልሆነ ግልፅ አቋም አለን ሲሉ ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሙሉ፤ “አሁን የትግራይ ህዝብ ችግር ላይ በወደቀበት ሁኔታ ይህ መደረጉት ትክክል አይደለም፤ ማኛውም የማንነት፣ የወሰን ጥያቄ ካለ ህግ እና ስርዓትን ተከትሎ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በህገመንግስቱ መሰረት ይፈታል ብለን እናምናለ” ብለዋል።
ችግሩ መፈታት ያለበት የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት በሚያጠናክር ግንኙነትን በሚያጎለበት መሆን አለበት እንጂ ከዚህ በኃላ በኃይል የሚባል ነገር አይሰራም ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለችግሩ መፍትሄ የሚሆነው ህግና ስርዓት ነው የሚል አቋም ይዟል፤ ሁኔታው ወደ ነበረበት እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጧል፤ በዚህ ላይም የፌዴራል መንግሥት ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመሳሳይ አቋም አላቸው ብለዋል። ሁሉም አካላት ችግሩ በህግና በስርዓት ይፈታ የሚል ተመሳሳይ አቋም ይዘዋል ሲሉ ዶ/ር ሙሉ ተናግረዋል።
የነበረው ኦፕሬሽን ህግን ማስከበር እንጂ ሌላ አልነበረም ፤ ችግሩን ለመፍታት መታየት ያለበት አብሮነትን በሚያጠነክር ሁኔታ እንጂ ከህግ ውጪ የሚሄድ ከሆነ ችግሩ የሚፈታ አይደለም።
ጥያቄም ለመጠየቅ ወቅት እና ጊዜ አለው ፤ አሁን የፌዴራል መንግስትም የያዘው ስራ ትግራይ የማረጋጋት ህግና ስርዓትን የማስከበረ ፣ ሰላም እና መረጋጋት የመፍጠር ነው ከዚህ ውጭ እየተፈጠሩ ያሉት ሁኔታዎች መስተካከል አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ መላው ትግራይ ከጫፍ እስከ ጫፍ (በዚህ ውስጥ ያለ ማንኛውም ኃይል) በመከላከያ ስር እንዲሆን አቋም አለው ብለዋል።
ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረግን እየሰራን ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
**
ዛሬ መጋቢት 1 በኢትዮጵያ የአሜሪካና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አምባሳደሮችን ጨምሮ 50 አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ተገኝተው ስለትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ገለጻ ተደርጎላቸዌ።
ዶ/ር ሙሉ የግጭቱ መነሻ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዙሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መውደቁን የገለጹት ዶ/ር ሙሉ በክልሉ የተፈጸመው የዘረፋ ተግባር “ህወሓት ከእስርቤት ፈቶ በለቃቸው ከ10ሺ በላይ ሰዎች”ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መጠገን፣ የክልሉን መንግስታዊ መዋቅር እንደገና መዘርጋትና ምርጫ ለማካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቀጣይ ተግባራት መሆናቸውን ዶ/ር ሙሉ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉ ዛሬ በነበረው ማብራሪያ እስካሁን 72 በመቶ በሚሆነው የክልል ግዛት መዋቅር መዘርጋቱና እስካሁን ያልተዘረጋበት ቦታ በአማራ ክልል ኃይሎች የተያዘው መሆኑንና ይህም መፍትሄ ያገኛል ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ልዩ ኃይል እና በሚሊሻ ስር ናቸው ስለተባሉት ቦታዎች የአማራ ክልል ምን ይላል ?

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያነሳውን ተደጋጋሚ ጥያቄ ከሰሞኑን የአማራ ክልል መንግስት በኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አማካኝነት ያዛዘውን አቋም በይፋ አስውቆ ነበር።
በዚህም የክልሉ አቋም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚያነሳው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው የሚል ነው።
አቶ ሙሉነህ ፥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጥያቄ የሚያነሳባቸው የወልቃይትና የራያ አካባቢዎችን በተመለከተ “ከመጀመሪያው በሕገ መንግሥት ወይንም በአዋጅ የተወሰዱ ቦታዎች አይደሉም” ያሉ ሲሆን፣ የክልሉ አስተዳደር የሚያቀርበው ጥያቄ ካለ ‹‹በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ›› ይችላል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል መንግስት አካባቢዎቹን እያስተዳደረው መሆኑን በመግለፅ የፌደራል መንግሥት በዘላቂነት መፍትሔ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡን እንደሚቀጥል ገልጿል።
