March 11, 2021

May be an image of 1 person

(ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም ባንክ ከፍተኛ አማካሪ አማካሪው ዶክተር አክሎግ ቢራራ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊ እና ገለልተኛ እንዲሆን ጠየቁ፡፡

ዶክተር አክሎግ ቢራራ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የያዘውን አቋም በተመለከተ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያ የተመድ መስራችና በሰላም ማስከበር ሂደቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የምታደርግ ሃገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የበርካታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቢሮዎች መቀመጫ መሆኗን ጠቅሰው፥ በአፍሪካ ለዘመናት የመረጋጋት፣ አካታችና ዘላቂነት ያለው ልማት ምሳሌ ሆና መቆየቷንም አውስተዋል፡፡

በደብዳቤያቸው በነጻና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት የመድብለ ፓርቲ ስርአት በመገንባት ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች ባለፉት ሶስት አመታት ሲካሄዱ መቆያታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ በመንግስት እየተወሰደ ያለው የማማሻያ ስራ ህወሓት ባደራጃቸው ሃይሎች እክል ገጥሞታልም ነው ያሉት፤ ለዚህም ቡድኑ ባለፉት 12 ወራት ብቻ 133 ብሄር ተኮር ግጭቶችን በገንዘብ ሲደግፍ እንደነበር ለማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ የሃገር ክህደት ወንጀልና ዘግናኝ ሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ያነሱት አማካሪው፥ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ግድያ እንዲሁም በማይካድራ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙንም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ የተደረጉ እንደ ማይካድራው አይነት ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን በመዘንጋት ለህወሓትና አጋሮቹ የወገኑበት አካሄድ አግባብ አለመሆኑንም አውስተዋል፡፡

አማካሪው በጻፉት ደብዳቤ ህወሓት ባለፊት 27 አመታት በአብዛኛው ወጣት የሆኑና በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በፀረ ሽብር ህግ ስም መጨፍጨፉንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ከሃገሪቱ በርካታ ቢሊየን ዶላሮችን በመዝረፍ ገንዘቡን ወትዋቾችን በመጠቀም የሃገሪቱን ስም ለማጥፋት፣ የሃሰት መረጃ ለመልቀቅና ለማወናበድ፣ ለበይነ መረብ ጥቃት ማስፈጸሚያ እና ለሰርጎ ገብ እንቅስቃሴና ለሚፈጸሙ ጥቃቶች መደገፊያ እየተጠቀመበት ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ህወሓት ኢትዮጵያን እንደ የመን፣ ሶሪያ ወይም ሶማሊያ የማድረግ አላማን ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር በደብዳቤያቸው የጠቀሱት አማካሪው ቡድኑ በኢትዮጵያ ከፈጸመው የሃገር ክህደትና ዘግናኝ ወንጀሎች አንጻር በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ባነሱት ሃሳብ የሶስትዮሽ ድርድሩ የአፍሪካ ህብረት ባስቀመጠው ማዕቀፍ መሰረት መቀጠል እንደሚገባው አውስተው፥ ከዚህ ባለፈም የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ አሜሪካና የዓለም ባንክ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገውም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፀጥታው ምክር ቤት የግብጽን ሃሳብና ፍላጎት ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት ሊያቆም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊና ገለልተኛ መሆን እንደሚገባው በመጥቀስም፥ አካሄዱን ሊያጤነው ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላይ ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ ማንኛውንም ማዕቀብ መጣል ችግሮችን ከማባባስ ያለፈ ሚና እንደለሌው በማውሳትም አካሄዱ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ይህን ተፈጻሚ ማድረግ በቀጠናው ለጽንፈኞችና አሸባሪዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ቀጠናውን ወደ አደገኛ ሁኔታ እንደሚከተውም አስጠንቅቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ መንግስት አስፈላጊውን የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እያደረሰ መሆኑን ያነሱት አማካሪው፥ በቀጣይም ድጋፉን እና የመልሶ ግንባታ ሂደቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ አለ ከተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን የማጣራት ሂደት እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በደብዳቤያቸው ማጠቃለያ በአየር ላንድ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ እቅድ የተዛባ እና ጥቁር አፍሪካውያንን ሊጎዳ የሚችል ነው ሲሉ የገለፁት ዶክተር አክሎግ መቼም ሊደገም አይገባም ብለዋል።

መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ብቸኛው ሃላፊነት ያለው አካል መሆኑን አንስተው የትግራይ ሁኔታም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም ነው ያሉት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊያከብሩ እንደሚገባ ጠቁመው፥ የትግራይ ክልል ነፃ ሀገር ሳይሆን የኢትዮጵያ አንድ አካል መሆኑን በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።

በመሆኑም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ከጣልቃ ገብነት ሊቆጠቡ እንደሚገባ እና የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳት ሊያስከትል ከሚችል አካሄዱ መታቀብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገው በትግራይ ክልል ብቻ እንዳልሆነና ተመድም ሆነ ሌሎች አካላት የኢትዮጵያ መንግስት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።