
የዩናይትድስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል «የዘር ማጥፋት» መፈጸሙን በተናገሩበት ወቅት በክልሉ የተፈጠረው ቀውስ እንዲመረመር እና የኤርትራ ወታደሮች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ግፊት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ብሊንከን በትናንትናው በኮንግረንስ አባላት ፊት ባደረጉት በዚሁ ንግግራቸው በክልሉ ግድያዎችን ጨምሮ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዩናይትድስቴትስ ተአማኒ መረጃ እንዳላት አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንኑ ማስቆም አለበት ብለዋል። ብሊንከን አያይዘው « ሕዝቡ ከዚህ በኋላ የዘር ማጥፋትንም ሆነ የሰብአዊ መብትን የሚጥሱ የጸጥታ ኃይሎችን ማየት የለበትም» ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከኤርትራ ወታደሮች በተጨማሪ የአማራ ክልል ኃይሎችም ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል። በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መደረግ አለበት ያሉት ብሊንከን በኢትዮጵያ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲኖራት አንዳች የእርቅ ሂደት እንዲደረግ እንሻለን ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል።
ዩናይትድስቴትስ እና ሌሎች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እያሳደሩ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቃወም በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በዩናይትድስቴትስ እና ካናዳ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። ሰልፈኞቹ በትግራይ ለተፈጠረው ቀውስ የቀድሞውን የክልሉን ገዢ ፓርቲ ሕወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል። DW
