13 መጋቢት 2021, 09:25 EAT

ክትባት የሚሰጠው ሰው

የአስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋትን ስለማስከተሉ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ባለመኖሩ በዚህ ስጋት አገሮች ክትባቱን ከመስጠት መቆጠብ የለባቸውም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ቡልጋሪያ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ ክትባቱን መስጠት ማቆማቸው መነገሩ ይታወሳል።

ይህንን በተመለከተ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ እንዳሉት በክትባቱ እና በደም መርጋት መካከል ምንም አይነት ግንኙነት የለም።

ማርጋሬት ሐሪስ እንዳሉት “እጅግ በጣም ጥሩ ክትባት” ስለሆነ ጥቅም ላይ መዋሉ መቀጠል አለበት።

እስካሁን ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ አውሮፓውያን የአስትራዜኔካ ክትባትን ወስደዋል።

አውሮፓ ውስጥ ክትባቱ ከተሰጠ በኋላ ወደ 30 የሚጠጉ የደም መርጋት አጋጣሚዎች መከሰታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ደም በሚመልሰውን የደም ሥር (ዲቪቲ) ህመምን ተከትሎ የ50 ዓመት አዛውንት ጣልያን ውስጥ መሞታቸውን የሚገልጹ ዘገባዎችም ነበሩ።

የዓለም የጤና ድርጅት ማንኛውንም የደኅንነት ጥያቄዎች የሚያከናውን በመሆኑ ሪፖርቶቹን እየመረመረ መሆኑን ሐሪስ ተናግረዋል።

ነገር ግን በክትባቱ እና በተዘገበው የጤና ችግር መካከል ምንም ምክንያታዊ ግንኙነት አልተገኘም ብለዋል።

አስትራዜኔካ አርብ ዕለት በክትባቱ ሰዎች ላይ የተመዘገበው የደም መርጋት “ከጠቅላላው ሕዝብ አንጻር ከሚጠበቀው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው” ብሏል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ክትባቱን ከወሰዱ “ከ10 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑት ላይ ያለን የደኅንነት መረጃ ትንተና ስጋቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ማስረጃ የለም” ሲሉ ገልጸዋል።

ቡልጋሪያ ክትባቱን ለማቆም የወሰነችው ዴንማርክ፣ አይስላንድ፣ ኖርዌይ እና ታይላንድ ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ተከትሎ ነው። ጣሊያን እና ኦስትሪያ በተወሰነ ጊዜ የተመረቱ ክትባቶችን ለጥንቃቄ እርምጃ በማለት መስጠት አቁመዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የመድኃኒት ተቆጣጣሪ የሆነው ዩሮፒያን ሜዲሲን ኤጄንሲ ቀደም ሲል እንደገለጸው ክትባቱ ለደም መርጋት ምክንያት ስለመሆኑ አንድም ማሳያ የለም።

እንግሊዝን፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ እና ሜክሲኮን ጨምሮ ሌሎች አገራት ክትባቱን መስጠት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የጀርመን ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የንስ ስፓን በበኩላቸው ክትባቱን ካገዱ አገራት ጋር እንደማይስማሙ ተናግረዋል።

“እስካሁን ካወቅነው አንፃር ጥቅሙ … ከጉዳቱ በእጅጉ የላቀ ነው” ብለዋል።

ጊዜያዊ እገዳው በአቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት ለተደናቀፈ የአውሮፓ የክትባት ዘመቻ ተጨማሪ እንቅፋት ሆኗል።

የኦስትሪያው ቻንስለር ሴባስቲያን ኩርዝ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገሮች የሕዝብ ብዛታቸውን መሠረት በማድረግ ለማከፋፈል እንደተስማሙት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን በፍትሃዊነት አያሰራጨ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

አንዳንድ አገራት ግዥውን ለአውሮፓ ኮሚሽን ከመተው ይልቅ ከክትባት አምራቾች ጋር የጎንዮሽ ስምምነትን መድረስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

የጀርመን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጥር ወር 30 ሚሊዮን ክትባት ከፋይዘር ባዮኤንቴክ ለማግኘት ስምምነት መፈራረሙን አምኗል።

አርብ ዕለት የዓለም የጤና ድርጅት ጆንሰን እና ጆንሰን የተባለውን እና አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን ክትባት አፀድቋል። የአውሮፓ ሕብረት ክትባቱን ሐሙስ ያጸደቀው ሲሆን አሜሪካ፣ ካናዳ እና በደቡብ አፍሪካ ያሉ ተቆጣጣሪዎችም ክትባቱን ደግፈዋል።

አውሮፓ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በቅርብ ወራቶች ስርጭቱ ከቀነሱ በኋላ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ቫይረሱ እንደገና ስርጭቱን እያሰፋ ነው። ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ እና ቱርክ ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግበዋል።

መላው ጣሊያን ወደ ጥብቅ አስገዳጅ የእንቅስቃሴ እገዳ እርምጃዎች ልትገባ ተዘጋጅታለች።

በዚህም ነዋሪዎች ለሥራ፣ ለጤና ምክንያቶች፣ ለአስፈላጊ ግብይት ወይም ለአደጋ ጊዜ ብቻ ከቤት መውጣት ይፈቀድላቸዋል። ሁሉም አስፈላጊ ያልሆኑ ግብይቶች እና እንደ ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ያሉት ዝግ ሆነው ይቆያሉ።

ትምህርት ቤቶች በበይነ መረብ ትምህርት የሚሰጡ ይሆናል ተብሏል።

በጣሊያን ውስጥ የሟቾች ጠቅላላ ቁጥር ሰኞ ዕለት ወደ 100,000 ከፍ ብሏል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት በአዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ምክንያት የበሽታው ስርጭት መጠን እየጨመረ ነው።