የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የፓርቲ ተሳትፎ እቃወማለሁ
[ በ ምስባክ ጳውሎስ ]

ዶ/ር ኢያሱ ኤልያስ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤት ክርስቲያን ፕሬዚዳንት ናቸው። አሁን ደግሞ በዚሁ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ይፋ ሆኗል።
የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የሚመሩትን ተቋም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንደሚወክሉ ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ቤተ ክርስቲያንን የገዥው ፓርቲ ወገን አድርጎ በማቅረብ፣ የፓርቲውንም ሆነ የመንግሥትን ውድቀት የቤተ ክርስቲያን ውድቀት ያደርጋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎችም የሌላ ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ አባላት ዘንድ ተቀባይነትና ከበሬታ እንዲያጡ ይዳርጋል። መሪዎች የፓርቲ ፓለቲካ ውስጥ ሲገቡ ሚዛናዊነታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ይህም የተለያዩ ውስብስብ ችግሮችንና የጥቅም ግጭቶችን ይፈጥራል። ከዚህ የተነሣ መሪዎች በሚወስዱት የተሳሳተ ወይም ወገንተኛ ውሳኔ የቤተ ክርስቲያን ተአማኒነት አደጋ ላይ ይወድቃል።
ስለዚህ እንኳን የአንድ ቤተ እምነት ፕሬዚዳንት ይቅርና የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ መደበኛ ባልሆነ መልኩ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የመሪነት ሚና ያላቸው ሰዎች በምንም መልኩ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለባቸውም!
ቢሆንልን ኖሮ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ከፓርቲ ፖለቲካ የቀጥታ ተሳትፎ ውጭ ሆነው ለፍትሕ፣ ለዕርቅና ለሰላም መሥራት ነበረባቸው። ከምርጫ ጋር የተነካካ ሚና ሊኖራቸው ከተገባም ምርጫን መታዘብን ከመሳሰሉ የምርጫ ሂደቱ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን ከሚያግዙ ሥራዎች ማለፍ የለባቸውም። የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በዚህ መልኩ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ግን እጅግ የሚያሳፍር ነው! ውድቀት ነው!
እናም ስለዚህ በይፋም ይሁን በስውር በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችም ከቤተ ክርስቲያንና መሪነትና ከፓርቲ ፖለቲካ አንዱን መምረጥ ይኖርባቸዋል።
ዶ/ር ኢያሱ ኤልያስም በቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካላቸው የትኛውም ዐይነት የመሪነትና የኀላፊነት ስፍራ እንዲለቁ እጠይቃለሁ!
ለነገሩማ የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያም ይህንን የሚፈቅድም አልነበረም!!
