March 15, 2021 10:13 am

በሲዳማ ክልላዊ መንግስት በግለሰብ ቤት ተከማችቶ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ከህብረተሰቡ የደረሰውን መረጃ መሰረት በማድረግ ለረጅም ጊዜ ሲከታተል ቆይቶ መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጭኮ ከተማ አስተዳደር እና በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ በርካታ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጎሳዬ ለገሰ ገልፀዋል፡፡

በጭኮ ከተማ ላይ በተደረገው ክትትል 30 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ እና ሁለት መትረየስ የተያዘ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ፋራ ቀበሌ ልዩ ቦታው ወልደ አማኑኤል ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኝ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የፌደራል ፓሊስ እና የክልሉ ልዩ ሀይል በጋራ ባደረጉት ፍተሻ 98 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ከ4,583 መሰል ጥይት ጋር እንዲሁም 3,546 የክላሽንኮቭ ጠመንጃ ጥይት ከሶስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ጎሳዬ ለገሰ ገልፀዋል፡፡(ኢቢሲ)