15/03/2021

የቋንቋ ነገር…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

 ለአዲሳባ ከንቲባነት ልወዳደር ወይስ ለክቡር ገና ልተውለት?   ምን ያንሰኛል?  ሌላው ቢቀር  ሁለት ቋንቋ   እችላለሁ – የአራዳና የገጠር አማርኛ አቀላጥፌ እናገራለሁ፤ 

የዛሬ አመት ገደማ ይመስለኛል: በካፒታል ሆቴል ጀርባ ባለው አቋራጭ መንገድ ሳልፍ ሁለት ጎረምሶች ይተናነቃሉ፤ ገባሁና ገላገልኩ፤ ሳጣራ አንዱ በቅርቡ ከታክሲ ረዳትነት የተቀነሰ ከተሜ ሲሆን ሁለተኛው ከገጠር የመጣ መፅሀፍ አዙዋሪ ነው፤ ምን እንዳጣላቸው ጠየኳቸው ፤

ከተሜው:-”  መፅሀፍ ልገዛው  በሰላም ቀረብኩት ፤ ጀለስ ለካ  የመጨረሻ ፋራ!   በቅርቡ በኮንትሮባንድ የገባች እንደሆነ  አላወቅሁም     የሾዳየን መጣመም  አለባበሴን ከልማ ሃንግ እምሰራት መሰላት፤  የሌለ   ተከመረችብኝ!  ጭራሽ  እንደ ቴርሞሜትር ቤቢቶውስ ከቶ አልጨመቀኝም!  በዚያ ላይ ፤  ጣራው የተነሳለት ቤተመፀሀፍት ተሸክሞ የሚውለው ክንዱ  የሌለ   ፌሮ ነው!   የቤቢቶው ኬሚካል  ሳይደፋኝ ደርሰህ ስለገላገልከኝ አመሰግናለሁ “ ወደ መፅሀፍ አዙዋሪው ዙሬ ” አንተስ ምን ትላለህ?”  

 -“አየ ጌታው! የመፀሀፍቱን  ነዶ አውርጀ  የጫማየን ሲባጎ ላጠባብቅ ጎንበስ ስል ይሄ ግንጭላም  የግንጭላም ልጅ  ተሁዋላየ መጥቶ ተዘበበ ! አልፎሃጅ ይሆናል ብየ ዝም አልኩት!  አድብቶ ዳናውን እንደ መብራት አጥፍቶ  ተጠጋኝ፤     ተጠጋኝና በጃኬቱ ኪስ  ስር  ባለ ብረት ጠቆም  አድርጎኝ  ! “ አባ ያለሽን ከቻሳ አድርጊው “ አለኝ፤  ውጥንቅጡ የወጣ አማርኛው    ባይገባኝም  ቀናለቀን ስዘርፍህ ተባበረኝ  ማለት  መሆኑን ግብኔ ነገረኝ ! ወይ አለመተዋወቅ ብየ በልቤ  ስቄ ዝም አልሁ!  “ አባው! ብቻየን እንዳልመስልሽ  ለጀለሶች   ምልክት ብሰጣቸው ከቻሳ ብለው አጉዋጉል ያደርጉሻል  እያለ ቀባጠረ ፤   እኔ በወገን  ልመካ ብል  አባይ ማዶ በጥይት ወፍ  የሚያረግፉ ዘመዶች አሉኝ፤ ግን ላንተ እኔ አላንስም!   እግዜርን ታልፈራሁ እንደ አደፈ ጨርቅ ጨፍጭፌ አሰጣሀለሁ  !  ለነፍስህ ካዘንክለት ተዚህ  ወግድ  ብየ ቁርጡን ነገርኩት!  እንዲህ አንድ አንድ ስንመላለስ ፤ጉርምቦየን ሊያንቀኝ ተንጠራራ፤   አልሞት ባይ ተጋዳይ ተጋፈጥሁት ! 

ብቻ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ብን ብሎ ጠፋብኝ !  የት ገባ ብየ  ወድያ ወዲህ ሳጣብር  ክርክርየ  (ብብቴ)  ስር ተሰንቅሮ አገኘሁት!  መጣህ ማርያም ታምጣህ ብየ ፤ ባለ በሌለ ሃይሌ   እንደ ተልባ ሳሸው   ፤ምላሱ እንደ ማግ ተጎለጎለ ! እርስዎ እንደ ሊቀ መላኩ ደርሰው ባያስጥሉት   ኑሮ በእጄ ላይ ጠፍቶብኝ ነበር!

  “ እኒህን አማርኞች አቻችላ የምትኖረውን አዲሳባን ለመምራት ከኔ በላይ ማን ይኖራል?

የሆነ ጊዜ ላይ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ ከተማ ጎበኘሁ፤ የተቀበለኝ ልጅ ጥሩ ልጅ ነው፤ አብረን ከሰነበትን በሁዋላ  ግን እንዲህ አለኝ  “ በውቄ! to be honest with you  እንግሊዝኛ ስትናገር እንደ ግእዝ ነው፤ስለዚህ የምትፈልገውን ነገር ለኔ ንገረኝና አስተረጉምልህለሁ”

 እየመረረኝ እሺ ብየ ተስማማሁ ፤

የሆነ ቦታ ስንደርስ ካፌ ውስጥ ይዞኝ ገባና

“ምን ልዘዝልህ አለኝ?

“ በጅንጅብል የፈላ ሻይ “ አልኩት፤  

ራሱን እያከከ ለረጅም ደቂቃ ቆየ ፤

ተግባብተናል፤

በመጨረሻ እንዲህ አለ፤

“ እዚህ አገር ጅንጅብል አያውቁም፤ ሌላ ነገር እዘዝ”