March 16, 2021

መደናገር በተፎካካሪው መንደር! – ዳንኤል ኪባሞ (ዶ/ር)

No photo description available.

ሲራራ – መጪው ምርጫ ከወዲሁ እንከን ያለበት ምርጫ መሆኑ እየታየ ነው። በኦሮሚያ ክልል የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ራሳቸውን ማግለላቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በኦሮሚያ ክልል እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ሕዝብ እንዳያደራጁና እንዳይቀሰቅሱ መደረጋቸው በምርጫው ፍትሐዊነት ላይ ከወዲሁ ጥላ የሚያጠላ ነገር ነው።

በመጪው ምርጫ የተሻለ ፉክክር እና አንጻራዊ ነጻነት ይታይበታል በተባሉት አዲስ አበባና አማራ ክልል ውስጥ ደግሞ የራሱ የተፎካካሪው ጎራ ትርምስ ብልጽግና የሚያሸንፍበትን ዕድል እያመቻቸለት ይመስላል። ብልጽግና ፓርቲ ጾታን፣ ሃይማኖትን፣ ብሔርን ወዘተ… ባገናዘበ መልኩ በርካታ ታዋቂ ሰዎችን በእጩነት አቅርቧል። የእሱን አቋም የሚደግፉ የግል ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል።

ሊተባበሩና ሊደጋገፉ የሚገባቸው ኢዜማና ባልደራስ በአንጻሩ ውስጥ ውስጡን የሚፈላ አውዳሚ የእርስ በርስ ቅስቀሳ ውስጥ ገብተዋል። ባልደራስ ከአብንና መኢአድ አብሮ መሥራቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖረው አማራ ውስጥ ቢያንስ የተወሰነውን እንዲያገኝ ያደርገዋል። ኢዜማም የዜግነት ፖለቲካን ስለሚያቀነቅን የራሱ መራጮች አሉት። ሆኖም ሁለቱም ፓርቲዎች ከሞላ ጎደል የሚቀራመቱት አንድን የኅብረተሰብ ክፍል ስለሆነ የድምጽ መከፋፈል መኖሩ ከወዲሁ እየታየ ነው። ሁለቱ ፓርቲዎች አብረው የማይሠሩ ከሆነ ብልጽግናንም አልመርጥም ሌላ ፓርቲም አልመርጥም ብሎ ራሱን ከመራጭነት የሚያቅበውም ቀላል አይሆንም። ይህ ሁሉ ለብልጽግና ይመቸዋል።

የተፎካካሪው ጎራ ራሱን ከምርጫው ማራቅም ሆነ እርስ በርሱ አለመናበብና መፎካከር መጪውን ምርጫ በዚህች አገር የዴሞክራሲ መሠረት የሚጣልበት እንዳይሆን ያደርገዋል።

ሲራራ-ሐሳብ!