ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ትናንት ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር ሊሄዱ ሲሉ የመንግሥት ደኅንነቶች እንዳገዷቸው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ መግለጻቸውን ፓርቲያቸው በፌስቡክ ገጹ ካሰራጨው ደብዳቤ ተመልክተናል፡፡ ለረጅም ጊዜ በውጭ ሀገር ሕክምና እንዳያገኙ በመከልከላቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ልደቱ ገልጸዋል፡፡ በተከሰስኩባቸው ወንጀሎች ነጻ መሆኔን ፍርድ ቤት ስለወሰነልኝ እና እገዳው የተጣለብኝ በፖለቲካ አመለካከቴ በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን እገዛ ያድርግልኝ ሲሉ ተማጽነዋል፡፡

