March 17, 2021

ግድቡ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውኃ የማይዝበት ምንም ምክንያት እንደሌለ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2013 ዓ.ም (አብመድ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውኃ የማይዝበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግድቡ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታና የግድቡን 10ኛ ዓመት የተመለከተ ውይይት ዛሬ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በዚህም ግድቡ ከወቅታዊ ሁኔታው፣ ከዲፕሎማሲ፣ ከማህበራዊና ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች አንጻር የሚኖረው ትስስር እንዲሁም ህጋዊና የቴክኒክ ጉዳዮችን የተመለከቱ የመነሻ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት የአምስት ዓመት ጊዜ በላይ በእጥፍ ጨምሮ በ10ኛ ዓመቱ የግንባታ አፈጻጸሙ 79 በመቶ ላይ ይገኛል።
የዲዛይን ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት፣ ተጨማሪ ሥራዎችና ሌሎችም ለግንባታው መዘግየት በምክንያትነት እንደሚጠቀሱ ነው የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የተናገሩት።
ፕሮጀክቱ በዘገየ ቁጥር የግንባታ ወጪውም በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ ገልጸው፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ አጠቃላይ ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ጠቁመዋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ለነበሩበት ችግሮች መፍትኤ በመስጠት ግንባታው እንዲፋጠን እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው ዕቅድ መሰረትም በዘንድሮ ክረምት ግድቡ ሁለተኛ ዙር ውኃ መያዝ የሚያስችለው ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።
“በዚህ መሰረት በመጪው ሐምሌና ነሃሴ ወራት ሁለተኛውን ዙር ውኃ ከመሙላት ወደ ኋላ የሚያስኬድ ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል።
የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትኤ መፍታት በሚለው መርህ መሰረት ሶስቱ አገሮች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ድርድር ማድረግ ጀምረው ነበር።
ይሁንና ድርድሩ መቋጫ ካለማግኘቱ ባለፈ ግብጽና ሱዳን ሶስተኛ ወገን ጣልቃ እንዲገባ እያሳዩት ያለውን ፍላጎት በተመለከተም “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፍትሔ እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት አላት” ብለዋል።
የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ሪፐፕሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት አማካሪዎችና የቴክኒክ ባለሙያዎች የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ በሚያደርጉት ጥሪ መሰረት የሶስትዮሽ ድርድሩ በቅርቡ እንደሚጀመር መገለጹን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m