March 18, 2021

የአውሮፓ ሕብረት የመድኃኒት ቁጥጥር ተቋም በኦክስፎርድ-አስትራዜኒካ የኮቪድ-19 ክትባት ላይ ባደረገው ምርመራ ክትባቱ “ደኅንነቱ የተጠበቀና ውጤታማ ነው” ሲል አስታወቀ።
የአውሮፓ የመድኃኒቶች ቁጥጥር ተቋም እንዳለው በክትባቱና የተለየ በሆነው በደም መርጋት መካከል ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ለማወቅ የሚያደርገውን ጥናት ይቀጥላል።
የሕብረቱ የቁጥጥር ተቋም እዚህ ውጤት ላይ የደረሰው 13 የአህጉሪቱ አገራት የሚያካሄዱትን የክትባት ዘመቻ ማቋረጣቸውን ተከትሎ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅትም አገራት የአስትራዜኒካ ክትባትን መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ መክሯል።
በርካታ የአውሮፓ አገራት ክትባቱን መስጠታቸውን ማቋረጣቸው ከክትባቱ አቅርቦት እጥረት ጋር ተዳምሮ በአህጉሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የክትባት ዘመቻ ሂደት ላይ ስጋት ፈጥሯል።
በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት መልሶ እያገረሸ ያለውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
- የአውሮፓ አገራት በአስትራዜኒካ ክትባት ጉዳይ ለሁለት ተከፍለዋል
- በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ መገኘቱ ይፋ በተደረገ በዓመቱ ክትባት መስጠት ተጀመረ
- ነፍሰጡር እናቶች የኮሮናቫይረስ ክትባት መውሰድ ይችላሉ?
- ስለኮሮናቫይረስ ክትባት ማወቅ ያለብን ወሳኝ ነጥቦች
የዓለም ጤና ድርጅት የክትባቱን ደኅንነት በተመለከተ እያካሄደ የነበረውን ምርመራ ውጤት ነገ አርብ ይፋ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
የአውሮፓ የመድኃኒቶች ቁጥጥር ተቋም ያደረገው ምርመራ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው ከክትባቱ ጋር በተያያዘ ተከስተዋል በተባሉት ትንሽ ቁጥር ባላቸው የተለየ የደም መርጋት ችግር ላይ ነው።
ታላላቆቹን የአውሮፓ አገራት ጀርመንን፣ ፈረንሳይንና ጣሊያንን ጨምሮ 13 አገራት ክትባቱን መስጠት ያቋረጡት የአህጉሩ የመደኃኒት ተቋም የሚያደርገው ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ “ለጥንቃቄ” ሲሉ የወሰዱት እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ከክትባቱ ጋር የተያያዘ ነው የተባለው የደም መርጋት በአገራቱ ውስጥ ክትባቱን ከወሰዱ በርካታ ሰዎች መካከል በጣም ጥቂት በሆኑ ሰዎች ላይ ነው የታየው።
የሕብረቱ ተቋም በክትባቱ ላይ ያገኘው ውጤት ላይ ተመስርቶ ክትባቱን መስጠት መቀጠሉን በተመለከተ ውሳኔውን የሚሰጡት አገራት ራሳቸው ናቸው።
የክትባቱ አምራች ኩባንያ የቀረበውን ስጋት ተከትሎ እንደገለጸው ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የጨመረ የደም መርጋት ችግር ስለመኖሩ የሚያመለክት ምንም አይነት ማስረጃ የለም።
በተጨማሪም አስካሁን በአውሮፓ ሕብረትና በዩናይትድ ኪንግደም ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ክትባቱን ቢወስዱም የተባለው የደም መርጋት ችግር አጋጥሟቸዋል የተባሉት ሰዎች ብዛት 37 ናቸው።
ክትባቱን የሰራው የኦክስፎርድ የክትባት ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሩ ፖላርድ ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት “አብዛኛው ክትባት በተሰጠባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተከሰተ ችግር አለመኖሩ የክትባቱን አስተማማኝነት የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።