19 መጋቢት 2021, 18:06 EAT

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አርማ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው እጃቸውን እንዲሰጡ ሌሎች ደግሞ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ሠላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት “ከሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ” በሚል በወጣው መግለጫ መንግሥት በህወሓት ላይ በወሰደው ሕግን የማስከበር እርምጃ የቡድኑ ወታደራዊ አቅምና ዝግጁነት በከፍተኛ ደረጃ መደምሰሱን ገልጿል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።

ለሦስት ሳምንታት በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ክልሉን የመንግሥት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ሲቆጣጠሩ የትግራይ ክልልን ለሦስት አስርት ዓመት ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት ከስልጣኑ ተወግዷል።

ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስታወቋል።

በወቅቱ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ ፓርቲው ሃይልን መሠረት ያደረገ የአመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን ማረጋገጡን ገልጾ ነበር።

የተካሄደውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከደረሰው ጉዳት በኋላ የክልሉን አስተዳደርና ልማትን ለማሻሻል የክልሉ ተወላጆች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቅሶ፤ ነገር ግን “አንዳንዶች በህወሓት ፕሮፓጋንዳና አሰገዳጅነት ነፍጥ አንስተው በውጊያ ሜዳ ላይ አስከመሰለፍ ደርሰዋል” ሲል አመልክቷል።

ጨምሮም መንግሥት እነዚህ ዜጎች ዋነኛ ፈጻሚዎች አይደሉም በማለት “ከዝርፊያና ከምዝበራው ተሳታፊ ያልነበሩና. . . በቡድኑ ቅስቀሳ መሳሪያ ታጥቀው የተሰለፉ በመሆናቸው መንግሥት ጉዳያቸው በሆደ ሰፊነት መታየት እንዳለበት ያምናል” በማለት ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

በመሆኑም በተፈጸሙ ጥቃቶችና ከዚሁ ጋር በተያያዙ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩና የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው የህወሓት ወታደራዊና የፖለቲካ አመራሮች በስተቀር ሌሎቹ ያለምንም የሕግ ተጠያቂነት በሰላም ወደ ኑሯቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

ለዚህመም መንግሥት የአንድ ሳምነት የጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ በክልሉ ላሉ የጸጥታ፣ የአስተዳደርና የሕግ አካላት መመሪያ መሰጠቱን ገልጿል።

በተጨማሪም ፈጽመውታል በተባሉ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩና ከፍተኛ ተሳትፎ አላቸው ተብለው እየተፈለጉ የሚገኙ የህወሓት ወታደራዊና የፖለቲካ አመራሮችም እጃቸውን በሠላም እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ ውጪ በተሰጠው የጊዜ ገደብ በቀረበው ጥሪ መሠረት ወደ ሠላማዊ ኑሯቸው ያልተመለሱና ተፈላጊዎችም ለሕግ አስከባሪ አካላት እጃቸውን ካልሰጡ “ሕግ ለማስከበር ሲባል አስፈላጊው ሁሉ የሚፈጸም ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋል።

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ በርካታ የህወሓት የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ላይ ቡድኑን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸምና በሌሎችም ወንጀሎች ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክህደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥረው የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ወራት ውስጥ የቀድሞ የህወሓት አመራሮችን ጨምሮ በአገሪቱና በክልሉ የሲቪልና ወታደራዊ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ በርካታ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎች ደግሞ መገደላቸው ተገልጿል።