
ግብፅና ብሪታኒያ በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ መምከራቸው ተነገረ፡፡
————————–
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል-ሲሲና የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ትናንት ሀሙስ ሌሊት በስልክ አድርገውታል በተባለው ውይይት የግድቡ የሦስትዮሽ ድርድር ዕልባት እንዲያገኝ መክረዋል ተብሏል፡፡
አል-ሲሲ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአባይ ጉዳይ ለግብፃዊያን ህልውና መሆኑን ለጆንሰን ነግረዋቸዋል፡፡
ግብፅ በወንዙ ላይ ያላት መብት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሳይነካባት የሦስቱም ሀገራት ጥቅም እንዲከበር እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡
በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት የግድቡ ጉዳይ ዕልባት እንዲያገኝ ሀገራቸው ግብፅና ሱዳን ፍላጎትና ተነሳሽነት ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ምክንያት እውን ሳይሆን እንደቀረ አንስተዋል፡፡
ይህ ተደጋጋሚ ሙከራ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ውድቅ ሲደረግ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
በቅርቡ እንኳን ሱዳን አቅርባዋለች የተባለውን አማራጭ ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም፡፡
አማራጩ የተባባሩት መንግስታት ድርጀት፣ የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካን ጨምሮ በድርድሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚጋብዝ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግን ይህ አማራጭ ተጎጂ እንደሚያደርጋት በመጥቀስ በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡
ግብፅና ሱዳን የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስምምነት ላይ ሳይደረስ መከናወን የለበትም በማለት በመወትወት ላይ ናቸው፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ በተያዘው ክረምት ሙሌቱ ላይከናወን የሚችለው ዝናብ ካልጣለ ብቻ ነው ስትል መገለፆ ይታወሳል፡፡
አሐዱ ራድዮ 94.3