22 መጋቢት 2021, 07:07 EAT

ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላት ግንኙነት መጠናከር ካለችበት ቀውስና እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ እየተፈጠሩ ካሉ ነገሮች ጋር ተያይዞ የተለያዩ አንድምታዎች እንዳሉት ተንታኞች እየተናገሩ ነው።
የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የቱርኩ አቻቸው ሜቭሉት ካቩሶግሉ በቱርክ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም “የተሳካ ተልዕኮ” በማለት ነበር አንድ ከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት የጠሩትት።
ቱርክና ኢትዮጵያ ይፋዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ የተገናኙት ሁለቱ ባለስልጣናት በዋነኝነት አጀንዳ አድርገው የተወያዩት ‘በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በተከሰተው የድንበር ይገባኛል ውጥረትና የደኅንነት ትስስራቸውን በማጠናከር’ ላይ እንደነ የቱርክ ዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ማሰቧ ‘ስልታዊ’ [ስትራቴጂክ] እንደሆነ የሚገልጹት ተንታኞች፤ ይህም በአፍሪካ ውስጥ ምጣኔ ሀብታዊና ወታደራዊ ግንኙነቷን እያጠናከረች ያለችው ቱርክ ሁሌም በሚቀያየረው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ የኃይል ሚዛን መመጣጠን ልትፈጥር እንደምትችልም ያምናሉ።
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ሚድል ኢስት ኢንስቲትዩት የቱርክ ጥናቶች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ጎኑል ቶል እንደሚሉት ቱርክ በውጭ ያላትን ተጽእኖ ለማስፋት እየሰራች እንደሆነ ነው። በተለይም ከ2015 (እአአ) ጀምሮ ያወጣችውን ፖሊሲ ተከትሎ ይህ እንደሚስተዋል ያስረዳሉ።
ቱርክና ኢትዮጵያ
በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እንዳሉት አገራት ኢትዮጵያና ቱርክ ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነቶች አላቸው። ምንም እንኳን በወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ወቅት ይህ ግንኙነት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም በኢህአዴግ መራሹም ሆነ አሁን ባለው አስተዳደር ቱርክና ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ግንኙነት አላቸው።
ለረዥም ዘመናትም ግንኙነታቸው በአብዛኛው በምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው። ለምሳሌ ያህል ቱርክ በኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሰሰችውን መዋዕለ ነዋይ ስንመለከት 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ይናገራሉ።
ይፋዊ የሆኑ ሪፖርቶችንም በምናይበት ወቅት በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ የምታፈሰው ቱርክ፣ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ደረጃ ከኃያሏ ቻይና ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱርክ ኩባንያዎች 20 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች አሏቸው። ይህም አሃዝ በአገሪቱ ውሰጥ ካሉ ግንባር ቀደም የግል ቀጣሪዎች መካከል እንደሚያስቀምጣት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ አስታውቋል።
- የሱዳን አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ምንድነው?
- የአሜሪካ ምርጫ የሕዳሴ ግድብ ፖለቲካን እንዴት ሊቀይር ይችላል?
- “የጦርነቱ መዘዝ ለቀጠናውም ይተርፋል” አወል አሎ (ዶ/ር)
በቱርክ መዲና አንካራ የኢትዮጵያ አዲስ ኤምባሲ ህንፃ በሚመረቅበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሜቭሉት ካቩሶልጉ፤ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ትግል አድናቆት ችረውታል እንዲሁም አገራቸው በዚህ ዘርፍ እንደምትተባበርም ቃል ገብተዋል።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለዘመናት በአብዛኛው በምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ ላይ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ደኅንነትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።

ቱርክ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት
በግብጽና በቱርክ መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ በሚመስልበት ሁኔታ የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት መጠናከር ዝም ብሎ የሚታይ እንዳልሆነ የዘርፉ ተንታኞች የሚናገሩት ነው። ለዓመታት ሊቋጭ ያልቻለው የህዳሴ ግድብ ድርድር የግብጽና ኢትዮጵያን ግንኙነት ውጥረት የነገሰ እንዲሆን አድርጎታል።
“ግብጽና ቱርክ ቁልፍ በሚባሉ የምሥራቅ ሜዲትራንያን የጋዝ ሃብትን በተመለከተ ወይም ሊቢያ ጉዳይ እንዲሁም በቅርቡም በሱዳን ጉዳይ ላይ ተፃራሪ አቋም ነው ያላቸው” የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኙ አብዱራህማን ሰይድ ናቸው።
ቱርክ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ስንመለከት ከአዲሱ የሱዳን አስተዳደር ጋር እየተቀየረ እንደሆነ አብዱራህማን ያስረዳሉ።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በስልጣን በነበሩበት ወቅት ቱርክ ከሱዳን ሱዋኪም የተባለችን ደሴት በሊዝ ተከራይታ ነበር። በቀይ ባሕር ላይ የምትገኘው ይህች ደሴት በቀጠናው ላይ ቁልፍና ስትራቴጂካዊ የምትባል ስፍራ ናት።”
“በሱዳንና በግብጽ እንዲሁም በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ ይመስላል። ሁለቱ አገራት ደግሞ ቱርክን ክፉኛ የሚቃረን አቋም ነው ያላቸው።
“ስለዚህም ቱርክ በሱዳን ላይ ያላትን ተፅእኖ በግብጽ ምክንያት እንዲሁም በተወሰነ መልኩ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ምክንያት አጥታዋለች” በማለት አብዱራህማን ያስረዳሉ።
በተቃራኒው በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ የሕግ መምህር የሆኑት አወል አሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ቱርክ አሁንም ቢሆን በሱዳን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ማድረግ እንደምትችል” ይናገራሉ።
አሁን ለምን?
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሰሜናዊ ክፍሏ ትግራይ ውስጥ በፌደራል መንግሥቱና በክልሉን አስተዳድር መካከል በነበረው ግጭት ምክንያት የተከሰተውን ቀውስ ለመቆጣጠር እየጣረች ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከሱዳን ጋር የድንበር ይገባኛል ውዝግብንም ገጥሟታል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል እያደረገች የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሱዳን በድንበር በኩል ሰፊ ግዛት እንደያዘች ተናግረዋል።
ጨምረውም ሁለቱን አገራት የሚያወዛግበውን ይህንን ግዛት ለመቆጣጠርም ሱዳንን እየገፋት ያለው “ሦስተኛ ወገን” ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
“የሱዳን መንግሥት ወታደራዊ ክንፍ የጫረው ግጭት ለሱዳን ሕዝብ የማይጠቅምና የሦስተኛ ወገን ፍላጎትን የሚያስፈጽም ነው” በማለት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቶ ነበር።
በሌላ ወገን ሱዳን በበኩሏ ባለው የድንበር ውዝግብ ውስጥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፋለች በማለት ብትወነጅልም ኤርትራ በበኩሏ ይህንን አትቀበለውም።
በርካታ ምዕራባውያን አገራት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት ተዛምቶ ቀጠናዊ ቀውስ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለፁ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ የወሳኝነቱን ቦታ የያዘችውና ቁልፍ ሚና መጫወት የምትችለው ሱዳን እንደሆነች ተንታኞች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በገጠሟት የተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት የተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላትን ትኩረት ስባለች። ተንታኞቹ እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ጠንካራ አጋሮች ያስፈልጓታል።
አወል (ዶ/ር) እንደሚሉትም ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ያላት ግንኙነት “አገሪቷ በአሁኑ ወቅት ከምትጋፈጣቸው ችግሮች ጋር የተያያዘ” እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህንንም ውሳኔ ስልታዊ [ስትራቴጂክ] እንደሆነም ይናገራሉ።
“ቱርክና ግብፍ መልካም ግንኙነት የላቸውም። ኢትዮጵያ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሱዳን ላይ ጫና ማሳረፍ ትፈልጋለች” በማለት ያስረዳሉ።
በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብን ለመፍታት ቱርክ የማደራደሩን ሚና ብትጫወት ኢትዮጵያ እንደምትቀበለው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቱርኩ ዜና ወኪል አናዶሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና ቱርክ ግንኙነት ወታደራዊ መልክ ይኖረው ይሆን?
ኢትዮጵያና ቱርክ በቅርቡ ምን አይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል የሚለው ግልፅ አይደለም። አወል (ዶ/ር) እንደሚያምኑት የሁለቱ አገራት ወቅታዊ ግንኙነት “በጥቅም የተሳሳረ” መልክ ያለው እንደሚመስል ነው።
ይህም ማለት ቱርክ በሱዳን ላይ ምን አይነት ጫና ታሳርፋለች ከሚለው ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ቢገልጹም ያ ለመሆኑ ግን ጥርጣሬ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አብዱራህማን በበኩላቸው ከትግራይ ቀውስና ከሱዳን ጋር ካለው ውጥረት ጋር ተያይዞ ድጋፉ ወታደራዊ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ።
“በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ከኢትዮጵያ ብዙ የራቀች አይደለችም። ለዚህ ደግሞ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ የጦር ሰፈርም አላት።”
“ቱርክ ወታደራዊው ዘርፍ በተለይም ድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላኖችን) በማምረት በኩል ጠንካራ አገር ሆናለች” የሚሉት አብዱራህማን በቅርቡም በአዘርባጃንና በአርሜኒያ መካከል በተደረገው ግጭት የቱርክ ድሮኖችን ጥቅም ላይ መዋላቸው እንዴት የጦርነቱን ውጤት እንደቀየሩት እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ።
“በዚህ በኩልም የኢትዮጵያ ፍላጎት ሊኖር ይችላል” በማለትም ያስረዳሉ።