የገዢው ፓርቲ አንድ አካል የሆነው የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተከሰተው ግጭት መነሻው “ጽንፈኝነት እና የፖለቲካ አሻጥር ነው” አለ።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሰኞ ማታ ባወጣው መግለጫ በአካባቢው ከአርብ ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት በንፁሃን ዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ሲል አስታውቋል።
የአማራ ክልል መስተዳደር ክስተቱን አስመልክቶ ቅዳሜ እለት ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ የሰዎች ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ጠቁሞ “በንጹሐን ላይ የተፈፀሙው ይህ ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው” ብሎ ነበር።
የአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች በንጹሐን ላይ የተፈጸመው ጥቃት አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው ማለቱ ይታወሳል።
የኦሮሚያ ብልጽግና በመግለጫው ላይ “የአማራ ክልል መንግሥት ታጣቂዎች፤ ያልታጠቁ ሰዎችን፣ እርቅ ሲሰብኩ የነበሩ ሽማግሌዎችን ሴቶችንና ሕጻናትን እንዲሁም ተጎድተው ወደ ሆስፒታል እየሄዱ የነበሩ ንፁሃንን በመግደል የወሎ ኦሮሞ ላይ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል” ሲል ወንጅሏል።
ፓርቲው አክሎም ጥፋተኞቹ “ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፤ ጉዳዩንም እንከታተላለን” ሲል አስታውቋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ የፀጥታና አስተዳደር ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ በበኩላቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተፈጠረው “ትክክል ነው ብለን አናምን” ሲሉ ተናግረዋል።
የቢሮው ኃላፊ ለቢቢሲ “የግጭቱ መነሻ ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረት ነው” ብለዋል።
ጉዳዩ ምንም እንኳ በአማራ ክልል ውስጥ የተፈፀመ ቢሆንም “ብሔር ተኮር ስለሆነ እኛንም ይመለከተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የጋራ አገር ነው ያለን፣ ሕግ ተጥሶ ንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ዝም ብለን ልንምለከት አንችልም፤ እናም ጉዳዩ ላይ እየሰሩ ካሉ አካላት ጋር በመሆን እየተከታተልነው ነው” ሲሉም አክለዋል።
በቅድሚያ ግጭቱ መቆም አለበት ያሉት አቶ ጅብሪል “ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ምንጩ ተጣርቶ ማስተካከያ መደረግ አለበት። የአማራ ክልል መንግሥትም ይህንን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ላይ ለግጭቱ መነሻ በማለት ስሙን ያልገለፀው አንድን ፓርቲ “ጽንፈኛ” በማለት ወነጀለ ሲሆን፣ “የክልሉ አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎችም ለሥልጣን ብለው የሰሩት አሻጥር ነው” ሲልም አክሏል።
በተጨማሪም በደረሰው ጉዳት ውስጥ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ፓርቲው አመልክቷል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በዚህ መግለጫው ላይ የግጭቱ መነሻ በኦሮሚያ ክልል ሁከት ለመቀስቀስ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ግጭት ማስነሳት እንደሆነ ይዘረዝራል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ መንግሥት ታጣቂዎች በንፁሃን ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ያደረሱትን ጉዳት አምርሮ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።
በዚሁ መግለጫ ላይ በዞኑ ውስጥ ኦነግ ሸኔ እንደማይንቀሳቀስ ገልጾ፣ “በንፁሃን ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመደበቅ ሲባል ሕዝቡን በኦነግ ሸኔነት መፈረጅ ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
የፖለቲከኞች አሻጥር ምክንያት በሕዝቦች መካከል ያለ ወንድማማችነት እንዳይጎዳ እና የአገር አንድነት እንዳይፈርስ ዜጎችን በንቃት መጠበቅ አለባቸው ሲልም አሳስቧል።
የተከሰተው ምንድን ነው?
ባለፈው አርብ ምሽት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፤ ኤፍራታና ግድም ወረዳና አጣዬ ከተማ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ የሠላምና የሕዝብ ደኅንነት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን አልታየ እስከ ቅዳሜ ረፋድ ድረስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል እያመለከቱ ነው።
የጅሌ ጥሙጋ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ሃሰን በበኩላቸው አጣዬና ጅሌ ጥሙጋ እንዲህ አይነት ግጭት ሲፈጠር የመጀመሪያ አይደለም በማለት ከባለፈው ግጭት በኋላ ሰላም ወርዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን የአንድ ግለሰብ መገደልን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት የክልሉ ልዩ ኃይል ለአንድ ወገን ሲያደላ ይታያል ሲሉ ይከሳሉ።
የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ለተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ ሐሙስ መጋቢት 9/2013 ዓ.ም ምሽት “ጅሌ ጥሙጋ ውስጥ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት መጥፋት” ለው ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ በአገር ሽማግሌዎችና በሐይማኖት አባቶች አማካይነት እርቅ ተፈጽሞ እንደነበር ጠቅሶ ነገር ግን “የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ” ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጿል።
በዚህም ከአርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ “አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል” ብሏል።
የአማራ ክልል እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ ላይ በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መጠን አልገለጸም።
በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተከሰተን ግድያ ተከትሎ ከአርብ በምሽት ጀምሮ ከባድ የተኩስ ድምጽ በአካባቢው መከሰቱንና በዚህም በርካታ ሰዎች እንደሞቱ ተነግሯል።
ግጭቱ ለተከታታይ ቀናት የቆየ ሲሆን በሰው ላይ ከደረሰው ቁጥሩ እስካሁን በውል ካልታወቀው ጉዳት ባሻገር በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በአካባቢው የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ግጭቶች አጋጥመው በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
ቢቢሲ