

24 March 2021
የአገሪቱ 65 በመቶ ክፍል በባለ ገመድ የኤሌክትሪክ መስመር ለማገናኘት እየተሠራ እንደሆነ የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ቅዳሜ መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጊንጪ ከተማ የተገነባው ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ጣቢያ በተመረቀበት ወቅት እንደገለጹት፣ ከ70 እስከ 75 ሚሊዮን የሚሆነውን ሕዝብ በገመድ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ለማገናኘት እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ከአገሪቱ 65 በመቶ የሚሆነውን ክፍል የሚሸፍን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ቀሪው 35 በመቶ የሆነው የአገሪቱ ክፍል ከገመድ ውጪ (Off Grid) የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚሆን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ይህም ታዳሽ የሆኑ የኃይል ምንጮች በመጠቀም የተራራቁ የመኖሪያ አካባቢዎችን የማገናኘት ሥራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት በዚህ ወቅት ያለውን 4,478 ሜጋ ዋት አጠቃላይ አገራዊ የማመንጨት አቅም ወደ 20,000 ሜጋ ዋት እንደሚያሳድግ የገለጹት ስለሺ (ዶ/ር)፣ ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኤሌክትሪክ ብርሃን ያገኛል ብለዋል፡፡
የጊንጪ – ደንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ መስመርን እንደ ምሳሌ ያነሱት ሚኒስትሩ፣ አሥር መውጫ መስመር ያሉት ጣቢያው ለአካባቢው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ አካባቢው ብዙ ኢንዱስትሪዎች የሌሉት በመሆኑ የኃይል ማከፋፈያው መገንባት፣ ኢንዱስትሪዎችና አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ሽቁጤ በተባለ አካባቢ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያ ግንባታ ለማከናወን የጥናትና የዲዛይን ሥራ እንደተጠናቀቀ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም የምዕራብ ሸዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን በማሳደግ በአካባቢው ሊቋቋሙ የታሰቡ የዕምነበረድ፣ የሲሚንቶና የማዕድን ፋብሪካዎችን ዕቅድ የሚደግፍ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ የኢነርጂ ልማት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚያሳየው፣ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ርዝመት በ2012 ዓ.ም. 18,400 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ ይህ ቁጥር በቀጣይ አሥር ዓመታት 29,900 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረገው የኢነርጂ መጠን በ2012 ዓ.ም. 2,803 ጊጋ ዋት ሰዓት (GWH) ሲሆን፣ በቀጣይ አገሪቱ 7,184 ለማድረስ እንደታቀደ ፍኖተ ካርታው ያሳያል፡፡