የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የተስተጓጎለውን የህዳሴ ግድብ ድርድር ለማስቀጠል መከሩ
የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የተስተጓጎለውን የህዳሴ ግድብ ድርድር ለማስቀጠል መከሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ሺስኪዴ ጋር በተወያዩበት ወቅት

ፖለቲካ

12 May 2021

ዮሐንስ አንበርብር

በግብፅና በሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ የገቡት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺስኬዲ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የህዳሴ ግድቡን ድርድር ለማስቀጠል በሚቻልበት አማራጭ ላይ ውይይት አደረጉ።

ፕሬዚዳንት ሺስኬዲ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንቀር በመሆናቸውና የህዳሴ ግድቡ ድርድር ቢስተጓጎልም ከአፍሪካ ኅብረት እጅ ጨርሶ ያልወጣ በመሆኑ፣ ወደ ሦስቱም አገሮች በማቅናት ድርድሩን ለማስቀጠል ያስችላል ባሉት አዲስ አማራጭ ላይ መወያየታቸው ታውቋል። 

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ያቀረቡት አዲሱ የድርድር አማራጭ ዝርዝር ባይገለጽም፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሥር የሚካሄድና ደቡብ አፍሪካም የምትሳተፍበት፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ የራሱን የመጨረሻ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርብበት እንደሚሆን ምንጮች ገልጸዋል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት እየተጫወቱ ያለውን ሚና ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የገለጹ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራና ለሦስቱም አገሮች ጠቃሚ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ቁርጠኛ እንደሆነች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለኅብረቱ ሊቀመንበር መግለጻቸውን አስረድተዋል።

አክለውም ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ሥር ከመካሄዱ ባለፈ፣ በሦስቱ አገሮች መሪዎች በተፈረመው የትብብር መርህ ማዕቀፍ (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) መሠረት ሊሆን እንደሚገባው መግለጻቸውም ታውቋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች መካከል የትብብርና የጋራ ልማት ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል፣ በሁለቱም አገሮች ላይ ምንም ጉዳት በማያስከትል መንገድ እንደሚከናወን ኢትዮጵያ ያላትን ፅኑ አቋምም አስረድተዋል።

ሱዳን የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ያቀረቡትን የድርድር አማራጭ እየመረመረችው እንደሆነ ስትገልጽ፣ ግብፅ በበኩሏ የዴሞክራቲክ ኮንጎን ጥረት እንደምታደንቅ በመግለጽ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት እንዲደረስ ያላት ፍላጎት ፅኑ መሆኑን አስታውቃለች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን ባለፈው ሳምንት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር መምከራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚያው ሳምንት ውስጥ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተመሳሳይ ውይይት ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጋር ማድረጋቸውና ከውይይቱ አጀንዳዎች መካከል የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።