ሜይ 18, 2021
- ቪኦኤ ዜና

ዋሺንግተን ዲሲ — ግጭት የተካሄደበት የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዘግናኝ ሁኔታ ተደቅኖበታል ሲሉ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ተናገሩ።
የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ ትናንት ሰኞ ጋዜጣዊ ጉባዔቸው ላይ በሰጡት ቃል በትግራይ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው፤ የጤና አገልግሎት ተቋማት ወድመዋል፥ አስገድዶ የመድፈር አድራጎት በብዛት እየተፈጸመ ነው፣ ያለውን ሁኔታ በአንድ ቃል ብገልጸው የሚዘገንን በጣም የሚዘገንን ነው የምለው” ማለታቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሀገሪቱ የመከላከያ ሃይሎች መቀሌ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ጦርነቱ መጠናቀቁን ካወጁ ከስድስት ወራት በኋም በቀጠለው ውጊያ በኢትዮጵያ ወታደሮች እና በአጎራባች ኤርትራ ወታደሮች የጅምላ ግድያዎች እና አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶች ይፈጸማሉ የሚሉ ክሶች እየቀረቡ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ሰብዓዊ ረድዔት በተለይም የምግብ ርዳታ የሚያስፈልገው መሆኑን ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረው ብዙ ሰዎች በረሃብ የተነሳ እየሞቱ ነው፤ አጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረቱ ተስፋፍቷል ብለዋል።
ብዙ መቶ ሽህ ሰዎች ከቀያቸው መሰደዳቸውን እና ከስድሳ ሽህ የሚበልጡ ደግሞ ወደሱዳን መሰደዳቸውን የዓለም የጤና ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።