May 20, 2021


አሳፋሪ ነው በሚል የተተቸው ስምምነት
————————–
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሰት ከታጣቂዎች ጋር ያደረገውን ስምምነት አስነዋሪ ተግባር ነው ሲል የቦሩ ዲሞክራሲ ፓርቲ ኮነነ፡፡

ፓርቲው ስምምነቱን የሁለት ሽፍቶች ስምምነት ሲልም ገልፆታል፡፡

ታጣቂው ቡድን ዜጎችን ሲያፈናቅል እና ሲገድል ከመቆየቱም በላይ የስልጣን ተጋሪ ለማድረግ የሚደገረው ጥረት አስነዋሪ ከመሆኑም ባሻገር ሰላማዊ ዜጎችን ወደ አመጽ ተግባር የሚመራም ነው ሲሉ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መብራት አለሙ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ያደረገው ስምምነት ህዝብን የናቀና ያላከበረ ስለ መሆኑም አመላካች ነው ብለውታል፡፡

ሊቀመንበሩ አያይዘውም መንግስት ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ ነው ብሎ በሚገልፅበት ስዓት በጎን ከሽፍታ ጋር መደራደሩ ደግሞ አፍራሽ እንቅስቃሴ በመሆኑ በፅኑ ያስወቅሰዋል ብለዋል፡፡

ፓርቲያቸውም ይህንን መሰረት የሌለውን የስምምነት ውሳኔ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንደሚያቀርበውም ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ስምምነቱ የተካሄደው በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ለመስጠት የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ አባላት ጋር ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡

አሐዱ የቤንሻንጉል ክልል መንግስት በቀረበበት ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ተደጋጋሚ ሙከራ እያደረገ ነው፡፡

አሐዱ ቴሌቪዥን