21 ግንቦት 2021, 10:01 EAT

በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ስምንት የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች መገደላቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ።
ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ከኅዳር ወር ወዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ ከተገደሉት የረድኤት ተቋማት ሠራተኞች ሰባቱ ግጭት ባጋጠመበት በትግራይ ክልል ውስጥ መሞታቸው ሲታወቅ አንደኛው ግን በሌላ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ መገደሉን ገልጿል።
የተገደሉት የእርዳታ ሠራተኞች ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለመደገፍ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ መሆኑን የኤምባሲው መግለጫ አመልክቶ፤ ድርጊቱን አጥብቆ አውግዞታል። እንዲህ አይነቱ ጥቃት እንዲቆም የጠየቀ ሲሆን ተጠያቂዎቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
በዚህም የአሜሪካ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ለረድኤት ድርጅቶች ሠራተኞች ህይወት እና ሥራ ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
መግለጫው ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ ሥራ የሚያከናውኑ ሠራተኞችን ጨምሮ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ዋነኛ ሚናው መሆኑን ጠቅሶ፤ የታጠቁ ኃይሎችም በዓለም አቀፍ የሰብአዊ አቅርቦት ሕግ መሠረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
- የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ
- የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ቅሬታ ያቀረበችባቸው ኃላፊው ከአገር እንዲወጡ ወሰነ
- ሁለት የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ትግራይ ውስጥ መገደላቸውን ገለጹ
- አምስቱ የትግራይ ክልል አስተዳደር ተግዳሮቶች
ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች የረድኤት ሠራተኞችና የሚያቀርቡት እርዳታ ደኅንነት ተጠብቆ ሳይገደብ፣ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ድጋፍ ለሚፈልጉ ለሁሉም ሰዎች እንዲደርስ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
በቅርቡ የተከሰተውን የእርዳታ ሠራተኛ ግድያ ያነሳው መግለጫ፤ የዩኤስኤይድ አጋር የሆነ ድርጅት ሠራተኛ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ትግራይ ቆላ ተንቤን ውስጥ “በኤርትራና በኢትዮጵያ ወታደሮች” መገደሉን ገልጿል።
መግለጫው የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንዳለው የእርዳታ ሠራተኛው በግልጽ የረድኤት ሠራተኛ መሆኑን በመግለጽ እንዳይገድሉት ሲማጸን እንደነበር አመልክቷል።
እንዲህ አይነቱ ሁኔታ “የእርዳታ ሠራተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በየዕለቱ እየተባባሰ ባለ የደኅንነት ሁኔታ ውስጥ እየሰሩ መሆናቸውንና አሳሳቢ የሰብአዊ እርዳታ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ቀውስን ያንጸባርቃል” ብሏል።
መግለጫው በማጠቃለያው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ በእርዳታ ሠራተኞችና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎቹን እንዲያወግዝና ምርመራ በማድረግ አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ አጥብቆ ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት በትግራይ ክልል ውስጥ “የከፋ ረሃብ” እንዳለ አስጠንቅቀዋል።
ኃላፊዋ እንዳሉት የአሜሪካ የአደጋ ጊዜ የምግብ አቅርቦት ክትትል ተቋም በአካባቢው “ደረጃ 5 የአደጋ ስጋት” እንዳለ መለየቱን ጠቅሰው ይህም ከፍተኛው እንደሆነ ገልጸዋል።
ሳማንታ ጨምረውም በክልሉ ያለው ግጭት እንዲቆምና ለእርዳታ ሠራተኞች መንገዶች እንዲመቻቹ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ውስጥ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል።