23 May 2021

ሲሳይ ሳህሉ

የመንግሥት ተቋማት በሮቻቸውን ለጋዜጠኞች ክፍት እንዲያደርጉ አሳሰበ

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን  ሕጉን ጠብቀው የማይሠሩ የሚዲያ ተቋማትን  በማባበል እንደማይቀጥል አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ጥፋት በሚፈጽሙ የሚዲያ ተቋማት ላይ በመረጃ የተደገፈ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ፣ ሕጋዊነት ላይ የሚኖር የድርድር ሒደት አይኖርም ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መሐመድ ኢድሪስ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የወጣውን ሕግ ለማስከበር ባለሥልጣኑ ‹‹ቆፍጣና›› ሆኖ ለመሥራት ዝግጁ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት የነበረው እንቅስቃሴ ልስላሴው የበዛ፣ ጥሰቶችና ግድፈቶች ሲያጋጥሙ ባለሥልጣኑ የሚሰጣቸውን የዕርምት ማስጠንቀቂያዎች  ወይም ግብረ መልስ እንደ ግብዓት ከመውሰድ ይልቅ፣ ውድቅ በማድረግ ባለሥልጣኑ መሳለቂያ የመሆን ደረጃ የደረሰቡት ሁኔታ እንደነበረ በመግለጽ፣ የሚዲያ ተቋማት ይህን ያህል ሲወርዱ ዝም ብሎ ማየት የባለሥልጣኑ ችግር እንደነበር ጠቁመዋል።

አቶ መሐመድ አክለውም መንግሥት ሚዲያውን ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት በመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ገልጿል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይየመንግሥት ተቋማትና አመራሮቻቸው በሮቻቸውን ለሚዲያ ተቋማት ክፍት በማድረግ ለሕዝብ መድረስ ያለበት መረጃ እንዲደርስ፣ ጋዜጠኞች ሊታገዙ እንደሚገባ አቶ መሐመድ አሳስበዋል፡፡

የመረጃ አሰጣጡ ተቋማት የፈለጉትን ጉዳይ ብቻ አዘጋጅተው መግለጫ በመስጠት  እንዲዘገብ መፈለግ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡

የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 11 ቀን 2013 .. አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ሚዲያዎች በሙሉ ሁነት ላይ እንዲዘግቡ የሚያደርግ  አካሄድ ስለሌላቸው፣ ከዚህ በተሻለ መንግሥት ለሕዝቡ የገባው ቃል ምን ደረሰ ብለው ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ለሚሄዱ ሚዲያዎች የተዘጉ በሮች መከፈት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የተሳሳተ መረጃን ማቆም የሚቻለው የመንግሥት አካላት ስለፈጸሙትና እየፈጸሙት ስላለው ሥራ፣ ሚዲያ ሲጠይቃቸው መልስ መስጠት ሲችሉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

‹‹ይሁን እንጂ ሚዲያው  በዘገባው በአገራዊ ጉዳዮች የማይደራደር መሆን አለበት። ሰላም ብሔራዊ ጥቅማችን ነው፤››  ብለዋል።

በተመሳሳይ ዜና ከዚህ በፊት ያልነበረውና በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት ሕጋዊ ሆነው እንዲመዘገቡና ፈቃድ እንዲያወጡ  የተደነገገባቸው የበይነ መረብ ሚዲያዎች ሕጋዊነት ምዝገባ፣ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2013 .የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል።

ነገር ግን ባለሥልጣኑ እንዲመዘገቡ ያወጣውን ጥሪ ተቀብለው የተመዘገቡ ጥቂት መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በተገባው ጊዜ የማይመዘገብ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ከግንቦት 15 ቀን በኋላ ሕገወጥ እንደሆኑ ይታወቅልን ሲሉ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የሃይማኖት ተቋማት ለሚዲያዎች በቅርቡ በሚደርግላቸው ጥሪ መሠረት ተመዝግበው፣  ሕግና ሥርዓቱን ጠብቀው መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል፡፡

በመጪው ሰኔ ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ሰዓት አጠቃቀም ለሕዝቡ ይዘውት በመጡት የፖሊሲና ፕሮግራም አማራጭ እርስ በርሳቸው እንዲከራከሩና ሕዝብ እንዲያውቅ ታስቦ የተመደበቢሆንም፣ፓርቲዎቹ ከዋናው ዓላማ በመውጣት መነቋቆርና መተቻቸት የበዛበት አካሄዳቸው መስተካከል እንዳለበት የባለሥልጣኑ የንግድ ብሮድካስት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዴሬሳ ተረፈ ተናግረዋል።

‹‹የተሻለ አገራዊ ፖሊሲን በሚገባ ከማስተዋወቅ ይልቅ አሁን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመተቸት  ለተጠመዱት ፓርቲዎች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ በተደጋጋሚ ይነገራቸዋል፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፖርቲዎቹ በዚህ ወይም በዚያ በኩል ይሂዱ ብሎ ማስገደድ አይቻልም፤›› ሲሉ አቶ ደሬሳ አክለው ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር