23 ግንቦት 2021, 13:23 EAT

አንዲት ሴት አልጋ ላይ የተኙ ታማሚን ስትመግብ
የምስሉ መግለጫ, ሕንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኮቪድ-19 ያገገሙ እና እያገገሙ ያሉ ህሙማንን በሚያጠቃው ‘ጥቁር ፈንገስ’ መያዛቸውን አረጋገጠች

ሕንድ ገዳይ በሆነው እና እየተስፋፋ ባለው የ’ጥቁር ፈንገስ’ በሽታ የተያዙ ከ8 ሺህ 800 በላይ ሰዎች መዘገበች።

እምብዛም ያልተለመደውና ሚዩኮማይኮስስ የተባለው ይህ በሽታ 50 በመቶ ገዳይ ሲሆን አንዳንዶችን ደግሞ የዓይን ብርሃናቸውን ያሳጣል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ ሕንድ ከኮቪድ-19 ያገገሙ እና እያገገሙ ያሉ ህሙማንን የሚያጠቃውን በሽታ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ አግኝታለች።

ሐኪሞች እንደሚሉት በሽታው ኮቪድን ለማከም ከሚጠቀሙት ስቴሮይድ መድሃኒቶች ጋር ይያያዛል።

የስኳር ህሙማንም ለዚህ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።

ሐኪሞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሽታው ሰዎች ከኮቪድ 19 ካገገሙ ከ12 እስከ 18 ባሉት ቀናት ይከሰታል።

በሕንድ በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የተመዘገበው በምዕራባዊ የሕንድ ግዛቶች ጉጃራት እና ማሃራሽትራ ነው።

ቢያንስ 15 ተጨማሪ ግዛቶች ከ8 እስከ 900 በበሽታው የተያዙ ሰዎችን መዝግበዋል።

የበሽታው ሥርጭት መጨመሩን ተከትሎም የሕንድ 29 ግዛቶች በሽታውን በወረርሽኝነት ሊያውጁ እንደሆነ ተነግሯል።

በአገሪቷ በበሽታው የተጠቁ ህሙማንን ለማከም አዲስ የተከፈቱ ማዕከላት በፍጥነት እየሞሉ ነው።

በማዕከላዊ ሕንድ ከተማ ኢንዶር በሚገኘውና 1 ሺህ 100 አልጋዎች ባሉት በማሃራጃ የሽዋንትሮ የመንግሥት ሆስፒታል ከሳምንት በፊት በቁጥር ስምንት የነበሩት ህሙማን ቅዳሜ ምሽት ቁጥራቸው ወደ 185 ከፍ ብሏል።

የሆስፒታሉ የሕክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ቪፒ ፓንደይ ከእነዚህ ህሙማን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፋጣኝ ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ በ’ጥቁር ፈንገስ’ የተጠቁ ህሙማንን ለማከም 200 አልጋዎች ያሉት 11 ክፍል ማዘጋጀቱንም ኃላፊው አክለዋል።

ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ወይም ሁለት በበሽታው የተያዙ ሰዎችን እንደሚያክሙ የተናገሩት ዶክተር ፓንደይ፤ አሁን ግን የበሽታው ሥርጭት መጨመሩ ያልተጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል።

የጥቁር ፈንገስ በሽታው ከኮቪድ-19 በበለጠ ፈታኝ ነውም ብለዋል ዶክተር ፓንደይ።

ህሙማኑ በሚገባና በቶሎ ሕክምናውን ካላገኙ የሞት ምጣኔው ወደ 94 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል ተነግሯል።

የሕክምናው ዋጋም ውድ እንደሆና በቂ የመድሃኒቱም አቅርቦት እንደሌለ ዶክተር ፓንደይ አክለዋል።

ዶክተር ፓንደይ ከአራት ሆስፒታሎች 201 ህሙማን መረጃ ሰብስበው ነበር። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ከኮቪድ-19 ያገገሙ እና ወንዶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

አብዛኞቹም በስቴሮይድ መድሃኒቶች የታከሙና እንደ ስኳር በሽታ ያሉ ተጓዳኝ ህመሞች ያሉባቸው ነበሩ።

በአራት ሕንዳውያን ዶክተሮች የተሠራ ጥናትም በሚዩኮማይኮስስ የተያዙ ከ100 በላይ የኮቪድ-19 ህሙማንን ተመልክቶ ነበር።

ከእነዚህ መካከል 79 የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 83 የሚሆኑት ደግሞ የስኳር ህመም ያለባቸው ናቸው።

በሁለት የሙምባይ ሆስፒታሎች በ45 የጥቁር ፈንገስ በሽታ ሕሙማን ላይ የተሠራ ሌላ ጥናትም በበሽታው የተጠቁት ሁሉም የስኳር ያለባቸው እንደነበሩ ወይም በስኳር ህመም ሳቢያ ተኝተው የሚታከሙ እንደነበሩ አመልክቷል።

በርካታ ሕሙማንን ያከሙ የዐይን ቀዶ ሕክምና ዶክተር አክሻይ ናያር “በሚዩኮማይኮስስ ከተጠቁ ህሙማን በደማቸው ውስጥ ጤናማ የስኳር መጠን ያላቸው አልነበሩም” ሲሉ ለቢበሲ ተናግረዋል።

ሚዩኮማይኮስስ ምንድን ነው?

ሚዩኮማይኮስስ ያልተለመደና በፈንገስ የሚመጣ በሽታ ነው።

በሽታው በአፈር ፣ በእፅዋት፣ በእንስሳት ጽዳጅ እና በበሰበሱ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ውስጥ ለሚፈጠረው ‘ሚዩኮር’ የተባለ ፈንገስ በመጋለጥ ይከሰታል።

የዐይን ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዶ/ር አክሻይ ኔር እንደሚሉት ሚዩኮማይኮስስ በማንኛውም ቦታ፣ በአፈርና በአየር እንዲሁም በጤማና ሰዎች አፍንጫና ንፍጥ ውስጥ ይገኛል።

በሽታው የፊትና የራስ ቅል መገጣጠሚያ አጥንቶች፣ አንጎል እና ሳንባ ላይ ጉዳት ያስከትላል።

የስኳር በሽታ አሊያም እንደ ካንሰርና ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች ያሉ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ የሆኑ ሰዎችን እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።