23 ግንቦት 2021, 09:34 EAT

አንዲት ሴት ክትባቱን ስትወስድ

የኮቪድ ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ በተለይ በሕንድ ይበልጥ ለተባዛው ገዳዩ ዝርያ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ክትባቶች ምን ያህል ፈውስ ይሰጡ ይሆን የሚለው ጥያቄ የጤና ዘርፉን ሲያስጨንቅ ነበር፡፡

አንድ ትኩስ ጥናት መልካም ዜና ይዞ መጥቷል፡፡

ፋይዘርና አስትራዜኒካ ክትባቶች ሁለት ጊዜ ከተወሰዱ የሕንዱን ዝርያ ተህዋሲ የመፈወስ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡

ሁለቱ የክትባት ዓይነቶች ሙሉ በሙሉ ከተወሰዱ (ሁለት ጠብታዎችን አከታትሎ መውሰድ) ክትባቶቹ ልክ ሌላውን የኮቪድ ዝርያ እንደሚከላከሉት ሁሉ የሕንዱን ዝርያም መከላከል ይችላሉ ተብሏል፡፡

ሆኖም ግን ሁለቱም ክትባቶች አንድ ጊዜ ብቻ ከተወሰዱ (አንድ ጠብታ ብቻ ከሆነ) የሕንዱን ተህዋሲ ዝርያ መከላከል የሚችሉበት ምጣኔ 33% ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ይህም ውጤት ከኬንት ዝርያ ያነሰ የመከላከል አቅም ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ሁለቱ ክትባቶች አንድ አንድ ጊዜ ቢወሰዱ የኬንት ዝርያን 50 ከመቶ የመከላከል አቅም መፍጠር እንደቻሉ ተደርሶበት ነበር፡፡

ጥናቱን ያካሄደው ፐብሊክ ሄልዝ ኢንግላንድ ሲሆን እነዚህ ክትባቶች የሟቾችንም ቁጥር ሆነ ሆስፒታል የሚመጣውን ታማሚ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንሱ አረጋግጧል፡፡

የዩኬ የጤና ሚኒስትር ማት ሐንኮክ ይህ ጥናት ትልቅ በራስ መተማመንን የሚፈጥር ነው ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል፡፡

ዩኬ በሰኔ መጨረሻ እቀባዎችን በከፍተኛ ሁናቴ ለማላላት የያዘቸውን ዕቅድም ነፍስ የዘራበት ጥናት ነው ማለታቸውን ተዘግቧል፡፡

ይህ ጥናት ያረጋገጠው ሌላው ነገር ቢኖር አስትራዜኒካም ሆነ ፋይዘር እጅግ ውጤታማ የመከላከል ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ሙሉ ጠብታ በሁለት ዙር መውሰድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡