የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ኃይሎችና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉን አስታወቀ።
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው ብሏል።
በዚህም መሠረት አሁን በሥልጣን ላይ ያሉም ሆኑ የቀድሞ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት የአሜሪካ ቪዛ እንዳያገኙ ዕቀባ መጣሉን ተገልጿል።
ይህ የጉዞ ዕቀባ ውሳኔ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉ ወይም የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዳይሳካ ያደናቀፉ የአገራቱን የደኅንነት ኃይል አባላትን ወይም የአማራ ክልልና ኢመደበኛ ኃይሎችንና ሌሎች ግለሰቦች እንዲሁም የህወሓት አባላትን የሚያካትን መሆኑ ተገልጿል።
ውሳኔው በተጨማሪም ትግራይ ውስጥ በሰዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጥቃት ፈጽመዋል በተባሉ ላይና በክልሉ ውስጥ የእርዳታ አቅርቦትን ባስተጓጎሉ ላይም ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፤ እርምጃው እገዳው የተጣለባቸው ግለሰቦች የቅርብ የቤተሰብ አባላትንም ሊመለከት እንደሚችል ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጨምሮም በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ለመግታት የቀረበውን ሐሳብ እንዳይተገበር ያደረጉ አካላት ተጨማሪ እርምጃዎች ከአሜሪካም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚጠብቃቸው ያሳሰበ ሲሆን ሌሎች መንግሥታትም ከአሜሪካ ጎን እንዲቆሙ ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ ላይ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ መውሰድ ያለበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ የጉዞ እገዳ በተጨማሪ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት ድጋፍ ላይ መጠነ ሰፊ ዕቀባ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።
ነገር ግን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጣቸው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቁልፍ የሆኑ ድጋፎችና የሰብአዊ እርዳታዎች እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
ኤርትራንም በተመለከተ ከዚህ በፊት ጥላቸው የነበሩ ሠፊ ዕቀባዎች ባሉበት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል።
መግለጫው በማጠቃላያው ላይ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ለተከሰተው ቀውስ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ለዚህም ጥረት አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጿል።
የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ መፍትሔ እንዲገኝ በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በኩል ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ልዩ መልዕከተኞች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳይን በቅረበት እንዲከታተሉላት አንጋፋውን ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማንን በልዩ መልዕክተኝነት ሰይማ ከሳምንታት በፊት በአካባው ጉብኝት አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንትም የአገሪቱ ሴኔት በትግራይ ግጭት ላይ ተሳታፊ በሆኑ ወገኖች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰድ የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አሳልፎ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በተደጋጋሚ በውስጥ ጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተጽእኖ ለመሳደር የሚሞክሮ መንግሥታትን ጫና እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ እና ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚያደርጉትን ጥረት የሚቃወም ሰልፍ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዶ ነበር።
በትግራይ ክልል ውስጥ ከስድስት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ አስካሁን የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በሺዎች የሚቆጠር ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ከዚህ ባሻገርም በግጭቱ ሳቢያ እዚያው በክልሉ ውስጥ የሚገኙና ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን የገቡ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸው ይነገራል።
በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተጀመረው ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ኃይሎች በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ሲከሰሱ ቆይተዋል።
ቢቢሲ