24 ግንቦት 2021, 07:03 EAT

በርካታ ወጣቶች በኤርትራ የነጻነት ትግል ውስጥ ተሳትፈዋል
የምስሉ መግለጫ, በርካታ ወጣቶች በኤርትራ የነጻነት ትግል ውስጥ ተሳትፈዋል

ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘች 30 ዓመት ደፈነች። የቀድሞው የቢቢሲ ትግርኛ አርታኢ የነበረው ሳሙኤል ገብረሕይወት ለነጻነቱ ነፍጥ አንግበው ከተዋደቁ ኤትራዊያን አንዱ ነበረ። ስለ ትግሉ እና እንደ ጉም ስለተነነው ኤርትራዊያን የነጻነትና ዲሞክራሲ ተስፋ እንዲሁም አገሪቱ እንዴት በአምባገነን እጅ ስር እንደወደቀች እንዲህ ይተርካሉ።

Short presentational grey line

ለሰላሳ ዓመታት ነፍጥ አንስተን ለነጻነት ተዋጋን፣ እያንዳንዱ ቀንና ሰዓት በጦርነት የሚያልፍ ነበር።

ስቃይንና መስዋዕት መሆንን ለመድነው። አብዛኞቻችን ሁለት ወይም ለሦስት ጊዜ ቆስለናል። ይህ ብርቅ አይደለም። እንደነገሩ ታክመን ወደ ሌላ ጦርነት እንዘምት ነበር።

በሰሜን ኤርትራ ቃሮራ ግንባርን እንዴት እንደታደግን ይገርመኛል። በደቡብ ኤርትራ ዱሜራን እንዴት እንደተከላከልን ይደንቀኛል። ምሽግ ለምሽግ እየተሳብን፣ እዚያው እያደርን፣ ተራራ እየቧጠጥን፣ ከሸለቆ ሸለቆ እየዘለልን…።

ብቻ እኔ ከዕድለኞቹ እመደባለሁ። 65 ሺህ ጓዶቻችን በጦርነቱ ሞተዋል።

የነጻነት ግንባሩን የተቀላቀልኩት በፈረንጆች 1982 ላይ ገና በ16 ዓመቴ ነበር።

ስለነጻነት ተዋጊ ኤርትራዊያን ብዙ እሰማ ነበር። ቁምጣቸው፣ ረዥም ጸጉራቸው፣ የሚይዙት ኤኬ 47 ጠመንጃ …፣ ይህ ሁሉ ታሪካቸው ያጓጓኝ ነበር።

በአራግ ሸለቆ ለጥቂት ወራት ስልጠና ተሰጠኝ። እንዴት ጥቃት መሰንዘር እንደምንችልና እንዴት ማፈግፈግ እንደሚቻል ተማርን።

እንዴት ራሳችንን ከአካባቢው ጋር ማመሳሰል እንደምንችል፣ እንዴት መደበቅ እንደምንችል፣ እንዴት ቦምብ ፈቶ መግጠም፣ ነቅሎ መጣል እንደሚቻል፣ አርፒጂ መሣሪያ አጠቃቀምን ሁሉ ሰለጠንን።

ስልጠናችን መጥፎ የሚባል አልነበረም። ጎን ለጎን ደግሞ የፖለቲካ ትምህርት እንደወስድ ነበር። ከዚህ መሀል እንዴት ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም እንደምንችል ጭምር ተምረናል።

ከዚህ ስልጠና በኋላ በበርካታ ጦርነቶች ውስጥ ተሳትፊያለሁ። መደምደሚያው የነበረው በ1990 (እአአ) በምጽዋ ወደብ ላይ የተደረገው ‘የፈንቅል ዘመቻ’ ነበር።

Samuel Ghebhrehiwet pictured in 2008
የምስሉ መግለጫ, ሳሙኤል ገብረሕይወት

ያ ድል እጅግ ወሳኝ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ከኤርትራ እንዲወጣም ያስገደደ ቁልፍ ወታደራዊ ድል ነበር።

ያን ጊዜ ያለማቋረጥ ለ72 ሰዓታት ተዋግተናል። እጅግ ወሳኝ የነበረችውን ምጽዋን ለመያዝ ያልሆነው የለም ማለት ይቻላል።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ለመከላከል 100 ኪሎ ሜትር ምሽግ ቆፍረን ከአንድ ዓመት በላይ ቆይተናል።

በዚህ ውጊያ ጭንቅላቴ ላይ እንዲሁም እጄ ላይ ቆስያለሁ። ከዚያ ሆስፒታል ታክሜ ዳንኩ። ታዲያ ወዲያውኑ ወደ ውጊያ ነበር የተመለስኩት።

በ1980ዎቹ መጨረሻ ወደ ኪነትና ባሕል ክፍል ተዛወርኩ።

የዚህ ክፍል ዋና ዓላማ ወታደሩን በሙዚቃና ድራማ ሞራሉን ከፍ ማድረግ፣ ማነሳሳት ነበር።

በ1991 (እአአ) ከምጽዋ ቅርብ ርቀት በዳሕላክ ደሴት ላይ ነበርን። ዳሕላክ ሳለን ነበር በሕይወታችን እጅግ ጣፋጩን ዜና የሰማነው።

ኤርትራ ነጻነቷን እንደተቀዳጀች ተነገረን።

የፈንጠዚያ ቀናት

በደስታ ሰክረን በጀልባ ወደ ምጽዋ ተጓዝን። እዚያ ስንደርስ ከባድ ተሸከርካሪ ላይ ተጭነን ወደ ዋና ከተማ አሥመራ ጉዞ ጀመርን። ጉዞው ሦስት ሰዓታትን የፈጀ ነበር።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ደቡባዊ ቀጠናን አለፍነው። ሰው የሚባል አልነበረም። የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥለውት ሄደዋል።

በአሥመራ ውስጥ ሕልም የሚመስል አውድ ነበር።

ነዋሪዎች እኛን የነጻነት ታጋዮችን ለመቀበል ጨርቄን ማቄን ሳይሉ አደባባይ ወጥተው ነበር።

በጓይላ ጭፈራ ራሳቸውን ስተው ነበር። ጎዳናው በሙሉ ሕዝብ ፈሶበት አስታውሳለሁ። ይህ በአሥመራ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችና መንደሮችም የታየ ኩነት ነበር።

ይህ ቀን ከመምጣቱ በፊት አሥመራ ሙሉ በሙሉ ጭንቅ ውስጥ ነበረች። አየር ማረፊያው በተከታታይ በተኩስ ሲናጥ ነበር የሰነበተው። ጥብቅ ሰዓት እላፊም ታውጆ ነበር። ልክ በግንቦት 24 (እአአ) ሁሉ ነገር ተለወጠ።

እናቶች የጣዱትን ጀበና ትተው፣ የለኮሱትን ሞጎጎ እንጀራ መጋገሪያቸውን ጥለው፣ የቡና ሥነ ሥርዓታቸውን ጣጥለው ግልብጥ ብለው አደባባይ ወጥተው ነበር።

ይህም እኛን ታጋዮችን ለመቀበል ነበር።

ብዙ ኤርትራውያን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ይታዩ ነበር። ወጣቶች እየዘለሉ ታንክ ላይ ይወጡ እንደነበረና የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለቡ ሲቀበሉንም አስታውሳለሁ።

ይህ ፈንጠዝያ ለቀናት ቀጠለ። ምሽቶቹም ደማቅ ነበሩ።

በእርግጥ በዚህ ደማቅ ስሜት መሀል ጭንቅም ነበረ። ወላጆች የልጆቻቸውን ፎቶ ይዘው በመውጣት በሕይወት ይኖሩ እንደሁ ይጠይቁ ነበር።

ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደ በኋላ እናቶች ደስታቸውን ሲገልጹ
የምስሉ መግለጫ, ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደ በኋላ እናቶች ደስታቸውን ሲገልጹ

“ልጄ ተርፎልኝ ይሆን? ልጄ ሞታ ይሆን?” የሚል የማያባራ ጥያቄ።

በኛ ምድብ ገድለና አባየይ የሚባሉ ጓዶች ነበሩ። ሁለቱ ጓዶች ፊት ለፊት በመኪና ላይ ተጭነው ቤተሰባቸውን ባዩ ጊዜ የሆኑት ትዝ ይለኛል፤ ሲጮኹ፣ ሲስቁ፣ የደስታ እንባ ሲያነቡ።

የገድለ አባት “ልጄን አገኘሁት! ልጄን አገኘሁት!” እያለ ወደኛ መኪና ሲሮጥ ትዝ ይለኛል።

አባየይ ደግሞ ሴት ታጋይ ነበረች። ጋቢና ነበር የተቀመጠችው። የባለቤቷን እናት ስታይ ጊዜ ድንገት እየሄደ ከነበረ መኪና ዘላ ልትወርድና ራሷን ለከፍተኛ አደጋ ልታጋልጥ ስትል ነበር በተአምር የዳነችው።

በኋላ ላይ በአዛዦቻችን ፈቃድ ተሰጠን፤ ፈቃዱ ወጥተን ቤተሰባችንን እንድናገኝ ነበር።

በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቤተሰብን ማግኘት ቀልድ አልነበረም። ለእነዚያ ሁሉ ዓመታት የተለዩትን ማግኘት እንዲህ የዋዛ አልነበረም። ሆኖም ብዙዎቻችን ዘመድ አላጣንም።

በዚያ ቅጽበት ሁላችንም እናስብ የነበረው ከዚህ ሁሉ በኋላ ኤርትራ በልጽጋ፣ ችግር ከኤርትራ ምድር ጠፍቶ እያንዳንዱ ኤርትራዊ በደስታና በፍሰሐ መኖር ይጀምራል የሚል ነበር።

ነገር ግን ይህ ተስፋችን እንደ ጉም ሊተን ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም።

የነበረንን ሁሉ ሰጠን፣ ለነጻነት ስንል። ወጣትነታችንን፣ ሕይወታችንን…።

ብዙዎቻችን ከነጻነት በኋላ ከውትድርና ተሰናብተን ቤተሰባችንን ተቀላቅለን፣ ትምህርታችንን ቀጥለን፣ ወደ ግል ሥራና ኑሮ ለመመለስ ነበር ዕቅዳችን።

ሆኖም ሠራዊቱን እንኳ ለመልቀቅ እንደማንችል ስናውቅ ተደነቅን።

ወታደራዊ አዛዦቻችን የፖለቲካ መሪዎች ሆኑ። አዲሲቷ አገር በእጇ ምንም ቤሳቤስቲ እንደሌላት ነገሩን። ኤርትራ ያላት ብቸኛ ሀብት የያዝናቸው የጦር መሣሪያዎች እንደሆኑ ተነገረን።

ከዚያ ሁሉ የጦርነት ፍዳና መከራ በኋላ የቀድሞ ተዋጊዎች ቀበቷችንን ይበልጥ እንድናጠብቅ በድጋሚ አረዱን።

ማንኛውንም ሥራ ያለ ክፍያ እንድንምንሰራ ነገሩን። ምግብ ብቻ ይሰጡናል። በነጻ እናገለግላለን።

ይህ ሁኔታ ለሁለት ዓመት ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ነው ትንሽ ገንዘብ ማግኘት የጀመርነው።

በትግሉ ጊዜ ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ ይተሳሰቡ የነበሩ ታጋዮች የመሪዎቹን እውነተኛ ባሕሪ ሲረዱ ተከፉ። ብዙዎቹ ወታደራዊ መሪዎች አገሪቱ ልክ ነጻ ከመውጣቷ አስረሽ ምቺው ውስጥ ገብተው ነበር።

በርካታ ታላላቅ አመራሮች በየመሸታ ቤቱ ይታዩ ነበር። ራሳቸውን እስኪስቱ ይጠጡም ነበር። በዚህ ወቅት ታጋዩ ኑሮው አለት ሆኖበት ነበር። የዕዝ ሰንሰለቱ እየላላ፣ መደበኛ ስብሰባዎች እየተረሱ መጡ።

መደበኛ ታጋዮች ነገሮች ከዛሬ ነገ ይስተካከላሉ ሲሉ ተስፋ አደረጉ፤ ገፋ ብለው ጠበቁ፣ ጠየቁ። አዲስ ነገር አልነበረም።

በርካታ ሴቶች በኤርትራ የነጻነት ትግል ውስጥ ተሳትፈዋል
የምስሉ መግለጫ, በርካታ ሴቶች በኤርትራ የነጻነት ትግል ውስጥ ተሳትፈዋል

ከጎረቤት ጋር አዲስ ጦርነት

እንደ አውሮፓውያኑ በ1993፣ የኤርትራ ነጻነት 2ኛ ዓመት ሊከበር ዋዜማ፣ የቀድሞ ተዋጊዎች አመጹ።

መሪዎቻቸው ብሶታቸውን እንዲያዳምጡም ተማጸኑ። መሪዎቻቸው ታላቅ ስብሰባ በአሥመራ ስታዲየም እንዲጠሩ አስገደዷቸው።

የተሰጠው ምላሽ ግን፣ “ችግራችሁ ይገባናል፣ የተለደመ ችግር ነው፤ ሁሉንም በቅርብ እንፈታዋለን” የሚል ነበር።

ልክ ይህ ስብሰባ እንዳበቃ ታዲያ መሪዎቹ የአመጹን አስተባባሪዎች አፍነው ወሰዱ። አንድ በአንድ።

በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ዓመት እስከ 15 ዓመት እንደተፈረደባቸው ሰማን።

የታጋዩን ችግር በይፋ በመናገራቸው ትልቅ ዋጋ ከፈሉ።

ብዙ “ሰዎች በቃ መሪዎቻችን ወደ አምባገነንነት ሊለወጡ ነው” ማለት ጀመሩ።

ሌሎች ግን ትንሽ መታገስና ማየት እንደሚገባ መከሩ። ኤርትራ እያረቀቀችው ያለው ሕገ መንግሥት ሲጠናቀቅ አገራችን ወደ ዲሞክራሲ እንደምታመራ ተነገረን።

ይህ ሁሉ ግን መና ቀረ። ኤርትራ በአንድ ፓርቲ የምትመራ፣ ምርጫ አካሄዳ የማታውቅ አገር ሆና ቀረች።

በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ኤርትራ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ጦርነት ውስጥ ገባች።

ከየመን በ1995፣ ከሱዳን በ1996፣ ከኢትዮጵያ በ1998 እና ከጂቡቲ ጋር በ2008። አዲሷ አገራችን ኤርትራ ሌሎች ተጨማሪ 10ሺህ ወጣቶቿን ሕይወት አስቀጠፈች።

አሁን የኤርትራ ወታደሮች ከነጻነት በኋላ በ5ኛው ዙር ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ። አሁን የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ነው። ከህወሓት ጋር ጦርነት ላይ ናቸው።

ህወሓት ኤርትራ ነጻነቷን ባወጀች ጊዜ ሥልጣን ላይ የነበረ ነው። ከ1998 እስከ 2000 ከኢትዮጵያ ጋር በተደረገው ጦርነት ወቅትም የነበረ ነው።

ከነጻነት በኋላ በነበረው ጊዜ ከገዢው ፓርቲ የባሕል ክፍል ውስጥ ገባሁ። ለታጋዮች የሚገባቸውን ሞገስ ለማሰጠት ብሎም አገሪቱን ለመገንባት ብዙ ሥራ እሠራለሁ በሚል ነበር።

በርካታ ተውኔቶችን፣ ሙዚቃዎችን ደረስኩኝ። ተሳትፌባቸዋለሁም።

ተወዳጇ ሔለን መለስ ‘ምጽዋ’ የሚለውን የኔን ሙዚቃ ተጫወተችው። ሙዚቃው ‘ምጽዋ ወድ ልጆችሽ የት ገቡ?’ የሚል ነበር።

ለውጥ አይቀሬ ነው

ትንሽም ቢሆን ጭል ጭል ትል የነበረችው የፖለቲካ ምህዳር ተስፋ የኢትዮጵያ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት ከሰመች።

መንግሥት ልወረር ነው የሚል ሥነልቦና በሕዝቡ ዘንድ ገዢ ሐሳብ እንዲሆን አደረገ። ይህ ጦርነት በጠረጴዛ ዙርያ ንግግር ብቻ እንዲቀር ማድረግ ይቻል እንደነበር ብዙዎች ያምናሉ።

በመስከረም 2001 (እአአ) ደግሞ መንግሥት ያልተጠበቀ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዘ።

አሥራ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና መካከለኛ ካድሬዎች ድንገት ዘብጥያ ወረዱ። ለዚህ የተዳረጉት ታዲያ አንዳንድ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ስለጠየቁ ብቻ ነው።

ከዚያች ዕለት ጀምሮ ሰዎቹ የት እንዳሉ ምንም አልተሰማም።

እነዚህን መሻሻል እንዲደረግ የጠየቁ ባለሥልጣናትን ያናገሩ፣ ስለነሱ የጻፉ 11 ጋዜጠኞችም ታስረዋል። ከነዚህ መሐል ወዳጄና ጓደኛዬ ስዩም ይገኝበታል። ስዩም ያኔ በድል ስንገባ ፎቶ ሲያነሳ የነበረ ልጅ ነው።

እነዚህ ሁሉ እስረኞች አንዳቸውም ፍርድ ቤት አልቀረቡም። አንዳቸውም ያሉበት አይታወቅም።

ኤርትራ አሁንም የአንድ ፓርቲ አገር ናት።

ከነጻነት ወዲህ ለ30 ዓመት ምርጫ የሚባል ነገር አድርጋ አታውቅም። ነጻ ፕሬስ የለም። ነጻ አደረጃጀት የለም። ሁሉም ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ የአገር ውስጥ ሲቪክ ድርጅቶች ታግደዋል።

ይፋ የሚደረጉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከነጻነት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ የጤናና የትምህርት አገልግሎት እንደተሻሻሉ ያሳያሉ። ይህን ማመን ግን ከባድ ነው።

ካለው ጥቂት የሥራ ዕድል እና አስገዳጅ እንዲሁም ክፍያ አልባ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጋር ተያይዞ በርካታ ወጣቶች አገሪቱን እየለቀቁ ነው።

በርካታ ወጣቶች በሌሎች የአፍሪካ አገሮችና በአውሮፓ ተጠልለው ይኖራሉ።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ብዙዎቻችን ተስፋ አልቆረጥንም።

ለውጥ አይቀሬ እንደሆነ በጽኑ እናምናለን።

ኤርትራ አንድ ቀን በሰማዕታት ቃል የተገባላትን የዲሞክራሲ ሕልም ትኖረዋለች።