May 25, 2021


May be an image of 1 person, sitting and suit

በተለያዩ መስኮች የተጀመረውን የሩስያ-አፍሪካ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናር እንደሚቻል እና ሀገራቸው ለዚህ ዝግጁ መሆኗን የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ እየተከበረ ያለውን የአፍሪካ ቀን በማስመልከት ለአፍሪካ ሀገራት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ፑቲን በመልዕክታቸው አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ላይ የተቀዳጁት ድል ለነጻነት፣ ሰላም እና ብልጽግና ያላቸውን ፍላጎት ያሳየ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

አፍሪካውያን በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ዘርፎች አስደናቂ ስኬቶችን አስመዝግበዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እየተጫወቱ ያሉት ሚና እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ቀጠናዊ ትብብሮችን በማሳደግ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን እና ቅንጅትን በመፍጠር እንደሚጠቅም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ሩስያ ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ዋጋ ትሰጠዋለች ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን የማይናወጥ ድጋፋችንን በመቀጠል አካባቢያዊ ግጭቶችን በመፍታት፣ ሽብርተኝነትን በመከላከል፣ ጽንፈኝነትን፣ የዕጽ ዝውውር እና ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል፣ እንዲሁም በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

እ.አ.አ በ2019 በሩስያ ሶቺ የተጀመረው የሩስያ -አፍሪካ ስብሰባ ላይ በተደረሰባቸው ስምምነቶች መሰረት ግንኙነቶችን ማሳደግ እንደሚቻል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል ሲል በኢትዮጵያ የሩስያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ EBC