ሜይ 26, 2021
- ቪኦኤ ዜና

ዋሺንግተን ዲሲ — ዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከትግራዩ ቀውስ ጋር በተያያዘ በአሁኖቹና በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉን ባሳለፍነው እሁድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን የቪዛ ክልከላውን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ፣
“በትግራይ ውስጥ ያለው ቀውስ እንዲፈጠርም ሆነ እንዲወሳሰብ በማድረግ ተጠያቂ በሆኑ ግለሰቦች፣ በአሁኖቹና በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም ለአማራ ክልል ኃይሎችና መደበኛና መደበኛ ላልሆኑ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ህወሓት/ አባላት፣ የቪዛ ማዕቀብ እንዲደረግ የተወሰነ መሆኑን አስታውቃለሁ” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በመግለጫው ይዘት እና በአቀራረቡ አዝነናል ያለው የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ክልል ለተከሰቱት ቀውሶች ብቸኛው መንስዔ ባሁኑ ወቅት የፈረሰው የህወሓት ቡድን እአአ ህዳር 3ቀን ያደረሰው አደገኛ ወታደራዊ ጥቃት አድራጎት ነው ሲል አሳስቧል። በማስከተልም ይህ በግዝፈቱ እና በክብደቱ ከዚያ ቀደም ባልተደረገ መልኩ የታቀደ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በቀደሙት ቀናት በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ይሁንታ የሰጠው ከመሆኑም በላይ በፓርቲው ቃል አቀባይ “ፈጥኖ ግቡን የሚመታ መብረቃዊ እርምጃ” ተብሎ በድፍረት ተገልጿል ሲል አክሏል።
ህወሓት በወታደራዊ ጥቃት ዕቅዱ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ኤርትራንም ጭምር ዒላማ ያደረገ እንደነበር ያመለከተው የኤርትራ መንግሥት መግለጫ የህወሓት ዓላማ ቢሳካ ኖሮ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሊያስከትል ይችል የነበረው እጅግ የከበደ አደጋና ትርምስ የታወቀ በመሆኑ ማብራራት አያስፈልገንም ብሏል።
አስከትሎም ይህን ሃቅ ለመሸፋፈን ኤርትራ ጥፋተኛ በማድረግ ጣትን መቀሰር ምክንያታዊም ተገቢም አይደለም ያለው መግለጫው ከዚያም በላይ መግለጫው በነጻነት በዓላችን ዋዜማ መውጣቱ ከመሰረታዊ ጭዋነት የወጣ ነው ብሎታል። በማስከተልም እርምጃው የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን ህግ አክባሪነትን አያራምድም፤ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም ጠቀሜታ አያመጣም ብሏል።