ምርጫ ቦርድ በእነ እስክንድር እጩነት ጉዳይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን እንደማይፈፅም መግለፁን ተከትሎ የባልደራስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ

ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ ሸዋ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት እነ አቶ እስክንድር ነጋን በተመለከተ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጩ እንዳይሆኑ ሰጥቶት የነበረውን ውሳኔ በመሻር እንዲመዘገቡ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።

በውሳኔው መሰረት የባልደራ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በዕጩነት ለማስመዝገብ እና እንደ ፍርዱ እንዲፈፀም ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ የተጠየቀ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ በፍ/ቤቱ የተሰጠውን ውሳኔ እንደማይፈፅም በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል።

ቦርዱ የዕጩዎች ምዝገባ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በመጠናቀቁን እንዲሁም እያንዳንዱ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖረውን ስፍራ የሚወስን ሎተሪ ዕጣ በመውጣቱና በዚሁ መሠረት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመትም ተጠናቅቆ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የመላኩ ተግባር በቅርብ ጊዜ የሚጀመር በመሆኑ እንደውሳኔው ለመፈጸም ቦርዱ የሚቸገር መሆኑን ነው የገለፀው። ይህን ተከትሎ የባልደራስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

ምንጭ_የባልደራስ ሚዲያ ክፍል