26 ግንቦት 2021, 11:16 EAT

ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሽረ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከተጠለሉት ተፈናቃዮች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በኤርትራና ኢትዮጵያ ሠራዊት ተወስደው መታሰራቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገለጹ።
ወታደሮቹ ሰኞ ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ ተፈናቃዮች ወደሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች በመሄድ ነበር ወጣት ወንዶችን መውሰዳቸውን የገለጹት።
በተለይ ፀሐየና ወንፊቶ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች ወንዶችን ከነበሩባቸው ክፍሎች በማስወጣት፤ አንዳንዶቹን በመኪና ሌሎቹን ደግሞ በእግር አሰልፈው እንደወሰዱዋቸውና ድብደባ እንደፈጸሙባቸው የዓይን እማኞቹ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተፈናቃዮቹን የማሰር “ተግባር ሊፈጽም እንደማይችል” በመግለጽ የተባለውን “ፈጠራ” ሲል አጣጥሎታል።
የሠራዊቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት ምላሽ “ሠራዊታችን በታሪክ እንዲህ አያደርግም። ይሄንን የሚገልጽ ዜናም የለም። ይህ ሊሆን የሚችልበት አግባብም የለም፤ ምን ፈልጎ ነው እንደዚህ የሚያደርገው?” ሲሉ ጉዳዩን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
ስለ ጉዳዩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ቴድሮስ አረጋዊ እስሩን በተመለከተ ማክስኞ ጠዋት መረጃ እንደደረሳቸው በመግለጽ “ሁኔታው ለምን እንደተፈጸመ እያጣራሁ ነው” ብለዋል።
- በትግራይ በወራት ውስጥ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ዩናይትድ ኪንግደም ስጋቷን ገለጸች
- ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስምንት የእርዳታ ሠራተኞች መገደላቸው ተነገረ
- የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የኬሚካል መሣሪያ ተጠቅሟል የሚለውን ዘገባ አስተባበለ
“አካባቢው ላይ ካሉ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች መረጃው ደርሶኛል። አስፈላጊ ማስተካከያ እንዲደረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገራለን” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ገልጸዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በትግራይ በተከሰተው ግጭት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተጠልሉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ ውስጥ ግድያና ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጽመዋል በመባል የተከሰሱ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ክሱን በተመለከተ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር ምርመራ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
በሽረ ከተማ ያጋጠመው ምንድን ነው?
ወይዘሮ ለምለም በጦርነቱ ምክንያት ከሞቀው ቤታቸው ተፈናቅለው በሽረ ፀሐየ ትምህርት ቤት ተጠልልው ከሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ናቸው።
ወታደሮቹ ሰኞ ምሽት 4፡30 አካባቢ እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ ለምለም “ሦስት ልጆቼን ወስደውብኛል። ብዙ ወጣት ናቸው በኃይል የተወሰዱት” በማለት የ18፣ 23ና 25 ዓመት ወጣት ልጆቻቸው መወሰዳቸው ተናግረዋል።
ወታደሮቹ የሁለቱ አገራት እንደሆኑና ወጣት ወንዶችን ብቻ ለይተው መውሰዳቸውንም ያስረዳሉ።
“ዓይነ ስውር ሳይቀር ደብድበዋል፤ ሴቶችን አንፈልግም ብለው ወንዶቹን ብቻ በሰባት መኪና ጭነው ወሰዱ። ተመልሰውም በእግር ብዙ ወጣቶች ወስደዋል” ብለዋል።
ወጣቶቹ የተወሰዱበትን ምክንያት በሚመለከት “የተነገረን ነገር የለም፤ ስናለቅስ ነው ያደርነው” ይላሉ።
የ78 ዓመት ባለቤታቸው እንደታሰሩ የሚናገሩት ሌላ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉትና ከዳንሻ የመጡ ተፈናቃይ በበኩላቸው፤ ወታደሮቹ ከፀሐየ ትምህርት ቤት ባለቤታቸውን መውሰዳቸውንና ጉና በሚባል መጋዘን ውስጥ መታሰራቸውን ይናገራሉ።
“የታሰሩበትን ምክንያት ለመጠየቅ ወደ ቀይ መስቀል ሄደን ነበር። አካባቢው ላይ ያገኘናቸው ወታደሮች እራሳችን ነው የወሰድናቸው፤ እዚህ ፎቶ በመነሳት የምታመጡት ነገር የለም። እራሳችን ለይተን እንለቃቸዋለን፤ ወደዚህ አትምጡ አሉን” ብለዋል።
በተጨማሪም “500 የሚሆኑ ሰዎች ነው የወሰዱት። ወጣት ይሁን አዛውንት እየደበደቡ ነው የወሰዱት፤ ብዙ ሰው ተደብድቧል” ሲሉም አስረድተዋል።
መንፊቶ ሌላው ተፈናቃዮቹ የሚገኙበት ቦታ ሲሆን በተመሳሳይ ሰዓት ሰዎች ተለይተው መወሰዳቸውን አንድ የዓይን ምስክር ገልጻል።
“መኪኖች መጥተው ግቢውን ከበቡት። ሰበሰቡን፤ አንዳንዶቹን በብትር መቱዋቸው። ጤነኞቹን በሙሉ ወሰዷቸው፤ ሁለት ሰዎች ብቻ ነው የቀረነው። እኛም አካል ጉዳተኞች ስለሆንን ነው” ብሏል።
“ትንሽ ይሁን ትልቅ ወንድ የሆነው ሁሉ ተወስዷል” የሚሉት የ60 ዓመቱ ተፈናቃይ አቶ ዘርአይ በበኩላቸው፤ ተመለሰው እንዳይመጡ በሚል ስጋት ስምንት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ይዘው ከማቆያው የወጡ እንዳሉ ተናግረዋል።
አንድ የ70 ዓመትና ሌሎች ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ የሚያውቋቸው ሰዎች መታሰራቸውም ገልጸዋል።
ባለሥልጣናት ምን አሉ?
በሽረ ከተማ 16 የስደተኞች መጠለያ እንዳለ የገለጸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ቴድሮስ አረጋይ “ትምህርት ቤቶች ላይ የነበሩ ተፈናቃዮች ማታ መወሰዳቸው መረጃው አለኝ” ብለዋል።
“ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ከዲስፕሊን ጋር የተያያዘ ከሆነ ወይም ያለመግባባት ካለ በማጣራት ይፈታሉ” በማለት፤ ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ እንደማያውቁና በጉዳዩ ላይ ክልሉን ከሚያስተዳድረው ‘ኮማንድ ፖስት’ ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ግን መረጃው “የፈጠራ” ነው በማለት አጣጥለውታል።
“የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደዚህ አይነት ተግባር ሊፈጽም የማይችል፤ ሰላም በማስከር በዓለም አንደኛ ደረጃ ሆኖ የሚቀጥል ነው” በማለት ተፈናቃዮችን የሚያስርበት ምክንያት የለውም ብለዋል።