የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግንቦት 13 በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በምርጫ የመወዳደር መብት አላቸው ወይስ የላቸውም በሚል ለወራት የዘለቀውን ክርክር በባለ ስምንት ገፅ ውሳኔ ዘግቶታል።
በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመልካችነት የቀረበውን አቤቱታም “በዕጩነት እንዳይመዘገቡ የሚከለከሉበት ሕጋዊ ምክንያት የለም” ሲልም ችሎቱ በይኗል።
የፓርቲው መስራች እና ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ እና የፓርቲው አባላት የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል እና ቀለብ ስዩም ከአንድ ዓመት በፊት የታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተፈጠው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
ግለሰቦቹ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ፓርቲያቸውን በመወከል ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በዕጩነት ለመመዝገብ ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር።
በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በዕጩነት ይመዝገቡልን የሚለው ጥያቄ ምንም እንኳን እንደ ባልደራስ ወደ ፍርድ ቤት አያምራ እንጂ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሲነሳ ቆይቷል።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በርካታ ለዕጩነት የሚቀርቡ አባሎቻቸው መታሰራቸውን አንስተዋል።
ኦነግ ከዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ በኋላ አባሎቼ ይፈቱ እንደሆነ በሚል ‘በእስር ላይ እያሉ ተመዝግበው ይቆዩልኝ‘ የሚል ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ አቅርቦ ነበር።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳም በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን በዕጩነት ለመመዝገብ የአገሪቱ ሕግ እንደማይፈቅድ መልስ ሰጥተዋል።
“እሱን በር ከከፈትነው የኦነግ አባላት ብቻ ሳይሆኑ በነፍስ ግድያ የተከሰሱትም ባይፈረድባቸውም በዕጩነት እንቅረብ ሊሉ ነው” ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ መልሰዋል።
“አንዳንድ አገራት ባልተለመደ መልኩ ይህንን ይፈቅዳሉ፣ የእኛ ሕግ ግን ያንን የሚፈቅድ አይደለም፤ ለምን ያንን አልፈቀደም ወደ ‘ሚለው መሄድ አልችልም፤ ግን ያንን የሚፈቅድ ስላልሆነ እስር ላይ ያሉ የፓርቲ አባላት በዕጩነት አይቀርቡም” ሲሉ ለኦነግ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል።
በሌላው ዓለም የታሰሩ ሰዎች ዕጩ መሆን ይችላሉ?
አደም ካሴ (ዶ/ር) በምርጫ ሕጎች ላይ ጥናቶችን ያደረጉ እና ኔዘርላንድስ ውስጥ መሰረቱን ባደረገው የዴሞክራሲ እና የምርጫ ድጋፍ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ባልደረባ ናቸው።
በዓለም ላይ የታሰሩ ሰዎች ለምርጫ ዕጩ መሆን ከአገር አገር ቢለያይም፤ በሕግ ጥላ ስር ሆነው ክስ ያልተመሰረተባቸው ሰዎች ግን በዕጩነት መመዝገብ መቻላቸው አጠያያቂ አይደለም ይላሉ።
“እንደ ሕንድ ያሉ አንዳንድ አገራት ተከሰው ያልተፈረደባቸው ሰዎች በምርጫ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ሕግ አላቸው። የተፈረደበት ሰው ግን ወጥቶ ሕዝብን ማገልገል ስለማይችል ይህ ቢከለከል ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።
በክስ ላይ ያሉ ሰዎችን በተመለከተ በሕግ ግልጽ ሆኖ መቀመጥ ነበረበት የሚሉት አደም፤ ይህ አለመሆኑ ምርጫ ቦርድንም ፈተና ውስጥ የሚከት ነው ይላሉ። አሁን ላይ ሕጉ በዚህ ረገድ ቢሻሻል ወደ ኋላ ተመልሶ አይሰራም ሲሉም ያስረዳሉ።
የፍርድ ሂደቱ ምን ይመስላል?
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሦስት አባሎቼ በዕጩነት ይመዝገቡልኝ ሲል ለየምርጫ ክልሎቹ አስፈፃሚዎች ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
በየክፍለ ከተማው ያሉ የቦርዱ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በሕግ ጥላ ስር ሆኖ ለዕጩነት መመዝገብ አይችሉም በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል።
ፓርቲው ውሳኔውን ለአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ያለ ሲሆን ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጥቶበታል።
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም “በእስር ላይ የሚገኝ ሰው የመንቀሳቀስ መብቱ ወይም ነፃነቱ የተገደበ ሰው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይችልም፣ ቢመረጥም ሕዝቡን ሊያገለግል አይችልም” በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ “በሕግ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ” የሚለው ሐረግ የዋስትና መብታቸው ተገፎ በማረሚያ ያሉ ሰዎችን ይጨምራል ወይስ አይጨምርም የሚለውን ተርጉሟል።
“ማረሚያ ቤት ውስጥ ያለ ሰው እንኳንስ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ፣ ከፈጣሪ የተሰጡ ሰብአዊ መብቶቹ፣ በተለይም የነፃነት መብቶቹ ተገድበው ያለ ዜጋ ነው” ይላል የችሎቱ ውሳኔ።
“በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በውጪ ካሉ ሰዎች ያነሰ መብቶች አሏቸው፣ ሕገ መንግሥቱ ስለተከሰሱም ሆነ ስለተፈረደባቸው ሰዎች በሚያስረዳበት ክፍሉ የመመረጥ መብት የሚያስረዳ አንዳች ነገር የለም” ሲል ውሳኔው ያትታል። አክሎም በምርጫ ሕጉ ላይ የተቀመጠው ክልከላ የሚያስረዳው የዋስትና መብት ተከልክለው በእስር ላይ ስላሉ እጩዎች የመወዳደር መብት ሳይሆን ከሕግ ከለላ ውጪ ስላሉ ሰዎች ነው ይላል።
ነፃ ሆኖ መገመት ማለት በወንጀል ክስ ወቅት ድርጊቱን የማስረዳት ሸክም ተከሳሽ ላይ እንደማይወድቅ ለማስረዳት እንጂ ተከሳሽ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን እንዲተገብር የሚፈቅድ አይደለም ሲልም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ አስቀምጧል።
የልዩነት ሃሳብ አለኝ ያሉት ዳኛ
ሙሉሰው ድረስ የተሰኙት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተሰየሙት ዳኞች በሁለተኛ ላይ የተቀመጡት ዳኛ በውሳኔው ባለመስማማታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የልዩነት ሃሳብ ይዘዋል።
“ሕግ ግልፅ በሆነ ግዜ ትርጉም አያስፈልገውም” የሚለውን ወርቃማ የሕግ አተረጓጎም መርኅን መሰረት አድርገው ልዩነታቸውን አስፍረዋል።
የምርጫ ሕጉ አንቀፅ 31 ለዕጩነት የሚያበቁ መመዘኛዎችን ያስቀምጣል ያሉት ዳኛው ከእነዚህም ውስጥም በሕግ ወይም በፍርድ የመመረጥ መብት መከልከል ተጠቅሷል ብለዋል።
ዳኛ ሙሉሰው እንዳሉት ቦርዱ የሕግ ወይም የፍርድ ቤት ክልከላን አላቀረበም፣ ሕጉም በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በዕጩነት መመዝገብ አይችሉም የሚል ክልከላ አላስቀመጠም ሲሉ ሞግተዋል።
ምርጫ ቦርድ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት የግለሰቦቹ የመመረጥ መብት መገፈፉን የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረበም የሚለው ለልዩነታቸው ዋነኛ ምክንያት ነው።
የሰበር ውሳኔ ምን ይላል?
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማለት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 80 መሰረት ከሕገ መንግሥት ውጪ ያሉ ሕጎች ላይ የመጨረሻ ትርጉም የመስጠት ስልጣን ያለው ችሎት ነው።
ችሎቱ ቢያንስ አምስት ዳኞች ይሰየሙበታል። በሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጡ ውሳኔዎች ይግባኝ የማይባልባቸው ብሎም ገዢ ናቸው።
ውሳኔዎቹም ከተሰጡበት ቀን ጀምሮ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች እንደሚተገበሩ በአዋጅ ተደንግጓል። ሰበር አስገዳጅ የሕግ ውሳኔ ሲሰጥም ታትሞ ይሰራጫል።
ታዲያ በባልደራስ እና በምርጫ ቦርድ ክርክር ላይም ይሄው ችሎት የመጨረሻ፣ ይግባኝ የማይባልበትን እና ገዢ ውሳኔ ሰጥቷል።
በባልደራስ አመልካችነት አቤቱታውን የተመለከተው የሰበር ሰሚ ችሎቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሕግ ስህተት አለበት ሲል ሽሮታል።
ለሰበር የቀረበው አቤቱታም በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን በዕጩነት ከመመዝገብ የሚከለክል ሕጋዊ ክልከላ የለም፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት የለውም እና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተከሰሱ ሰዎች በሕግ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብትን ይፃረራል የሚሉ ናቸው።
ችሎቱ በቅድሚያ የተመለከተው ምርጫ ቦርድ የሰበር ሰሚ ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ስልጣን የለውም ሲል ያቀረበው መከራከሪያ ላይ ነው። ሕጎችን በማጣቀስ ማንኛውም የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሕግ ጥሰት ካለ የመመልከት ስልጣን አለኝ ሲል ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
ችሎቱ አንድ ሰው የመምረጥ እና የመመረጥን ጨምሮ ሕዝባዊ መብቶቹ በፍርድ ቤት ለተወሰነ ጊዜም ይሁን ለዘወትር ሊከለከሉ እንደሚችሉ ውሳኔው ያትታል።
የወንጀል ሕጉን ድንጋጌዎች በመጥቀስ ከሞት ፍርድ እና የፅኑ እስራት ቅጣት ውጪ ከሕዝባዊ መብት መሻር እንደ ተጨማሪ ቅጣት የሚወሰድ፤ ፍርድ ቤቱ የጥፋቱን ክብደት እና የጥፋተኛውን ባህርይ በማየት የሚወስነው መሆኑን ያብራራል።
ከፍርድ በፊት ነጻ ሆኖ መገመት ማለት ተከሳሹ በሕግ በግልጽ ያልተከለከሉ መብቶቹ እንዳይነኩበት አላማ የያዘ ነውም ይላል።
“ዕጩው የመንቀሳቀስ መብቱ ተገድቦ ሳለ የምርጫ ቅስቀሳን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ማካሄድ ስለማያስችለው” በሚል ከቦርዱ ለመጣው አቤቱታ ችሎቱ መልስ ሰጥቷል።
“ዕጩው የቀረቡት በፓርቲው በመሆኑ የምርጫ ቅስቀሳው በዋናነት የሚሰራው በፓርቲው በኩል መሆኑን መገንዘብ አስቸጋሪ ካለመሆኑ ባሻገር፤ በዚህ ረገድ የቀረበ አቤቱታ በሌለበት የስር ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው መሰረት ማድረጉ አግባብ አይደለም” ሲል መከራከሪያውን ውድቅ ያደርጋል።
ሰበር ሰሚው የምርጫ ሕጉን በመጥቀስ የመምረጥ መብታቸው ያልተከለከለ እና በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች የመምረጥ መብታቸው እንዲጠበቅ ልዩ ሥርዓት ተዘርግቷል ሲል ያስረዳል። “ይህም ለዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን እና የሚበረታታ መሆኑን ያሳያል ነው” ሲል ችሎቱ ያክላል።
የሰበር ሰሚ ችሎቱ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው፣ ሊታረም ይገባል ሲል ውሳኔውን ሰጥቷል።
በቀጣይ ወዴት ያመራል?
ከዚህ ቀደም በእስር ላይ ያሉ አባላቶቻቸውን በተመለከተ በስብሰባዎች ላይ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ፓርቲያቸው በዚህ ውሳኔ መሰረት የሚያቀርበው ጥያቄ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“አጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ ስለተበላሸ ለእኛ ይሄ ብዙ ጥቅም የለውም። ከ200 በላይ ቢሮዎቻችን ተዘግተውብናል። ያለፈው ዓመት ሚሊዮኖችን የምንሰበስብበት ጊዜ ነበር” ብለዋል።
“እኛ አጠቃላይ ምርጫው ምርጫ መሆን ስለማይችል ነው የወጣነው” ሲሉም አክለዋለ። “የኔ ስጋት የፍርድ ቤት ነፃነት እንዳለ ለማስመሰል እንዳይሆን ነው፤ ከልደቱ ውጪ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሲከበር አላየንም” ያሉት መረራ “ለልጆቹ [ለባልደራስ አባላት] ግን ሞራል ይሰጣል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ የሚለዩት አደም ይህ ውሳኔ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን እምነት የሚጨምር ነው ይላሉ። ነገር ግን እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች በፍጥነት አለመስተናገድ የሚያመጣውን ጫናንም ያሳያል ብለዋል።
አደም በኦሮሚያ ክልል የሚወዳደሩት ሁለቱ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ እንዲያነሱ እድል የሚሰጥ ውሳኔ መሆኑንም ያብራራሉ።
“እነዚህ ፓርቲዎች በዕጩዎቻቸው መታሰር በምርጫው ፍትሃዊነት እና ተአማኒነት ላይ ሲያነሱ የነበረውን ጥያቄ ወደ ሕጋዊነት ጥያቄ ይወስደዋል። ‘እኛ ያቀረብናቸው ሰዎች ያላግባብ ከመወዳደር ስለተከለከሉ ሕጋዊነት የለውም‘ ብሎ ከምርጫው በኋላ ክርክር ማንሳት የሚያስችላቸው ውሳኔ ነው” ሲሉ አደም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቦርዱ ሁለት ሕጋዊ አማራጮችን ሊከተል እንደሚችል የሚናገሩት አደም የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥልኝ ብሎ ለአጣሪ ጉባኤው ማመልከት አንዱ ነው። ይህ በተለይ ከምርጫው በፊት ባለው ቀሪ ጊዜ ውስጥ የሚሆን እንደማይመስላቸው ያብራራሉ።
“ቦርዱ ይህንን ውሳኔ መቀበል፣ ካልሆነ ደግሞ ዕጩዎቹ በውሳኔው መሰረት መብት እንዳላቸው ገልፆ፤ ነገር ግን ይህንን ለመፈጸም የማይችልበትን ምክንያት አስረድቶ በዚህ ምርጫ ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን ውሳኔ (declaratory judgment) መጠየቅ ይችላል” ሲሉ የሕግ ባለሞያው ያስረዳሉ።
ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤት የታዘዘውን በሌላ በምንም ምክንያት አልፈጽምም ማለት እንደማይችል የሚያብራሩት አደም ይሄ መንግሥት በተደጋጋሚ እየተወቀሰበት ካለው የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ያለማክበር ጋር ተመሳሳይ እና አጠያያቂ ያደርገዋል ይላሉ።
እንደ መውጫ
ይህ ውሳኔ የሚተገበር ከሆነ በቦርዱ ሎጂስቲክ አቅርቦት ላይ ጫና ያመጣል የሚሉት አደም ይህም የዕጩዎች ዝርዝር የያዙ ሰነዶችን ማረም ይጠይቀዋል ይላሉ።
“በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ፣ በተለይም በአሮሚያ ያሉ ፓርቲዎች ክስ የሌለባቸው ይሁን ያለባቸው ‘ዕጩዎቻችን ይመዝገቡልን‘ ብለው ሲጠየቁ እንደማይችሉ ምላሽ ተሰጥቷቸው ነበር” ሲሉ አደም ያስታውሳሉ።
አደም ይህ ውሳኔ ከሕጋዊ አንድምታው ሌላ የፖለቲካ አንድምታ እንደሚኖረው ያብራራሉ። ፓርቲዎቹ አሁን ዕጩዎቻቸውን ባያስመዘግቡ እና ለውጥ ባያመጡም የምርጫው ሕጋዊነት ላይ የሚያነሱትን ወቀሳ እንደሚያጠናክረው ይናገራሉ።
“በአጠቃላይ ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረው ይህ ውሳኔ የምርጫው ቅቡልነት እና ፍትሃዊነት ላይ ብቻ ሳይሆን ሕጋዊነቱ ላይ ጭምርም ጥያቄ ሊያስከትል ይችላል” እንደ ባለሞያው መደምደሚያ።
አደም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተቋማት መካከል እርስ በእርስ በሕግ የመፈታተን እንዲሁም ራሳቸውን የቻሉ ተቋማት መጠንከር እና ጠንክሮ መቆምን የሚያሳይ እንደሆነም ያክላሉ።
ቢቢሲ