የትግራይ ቴሌቭዥን በትግራይ የተቀሰቀሰዉ በጦርነቱ ምክንያት ስርጭታቸዉ ከተቋረጡ ሚድያዎች አንዱ ነበር። የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልል በጊዚያዊ አስተዳድር እንዲመራ ሹሞኞች ከሰየመ በኋላ የትግራይ ቴሌቭዥንም በአዲስ አመራር ስርጭቱ እንዲጀምር ተደረጎ ነበር።

መቐለ በሚገኘዉ ነባሩ ስቲድዮ ስርጭቱ እያስተላለፈ የነበረ ሲሆን ሚያዝያ 13ቀን 2013 ዓ.ም ላይ ስርጭቱ መቋረጡም የሚታወስ ነው።

አዲሱ የትግራይ ቴሌቭዥን ስራ አስፈጻሚ ሆነዉ የተሾሙት ጋዜጠኛ ካሕሳይ ብሩ የጣብያዉ ስርጭት የተቋረጠዉ ከእዉቅናችን ዉጪ በሆነ መንገድ ነበር ይላሉ፡፡

ይህንን በተመለከተ የጣብያዉ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ ለስብሰባ ተጠርተዉ ጣብያዉ ለዉጥ ስለሚያስፈልገዉ የሚደረገዉ ለዉጥ በተመለከተ ዉይይት አድርገዉ በቴሌቭዥኑ የሚደረገዉ ለዉጥ በሚመለከት አቶ አርአያ ተስፋማርያም እንዲያስተባብሩ መሾማቸዉ ጋዜጠኛ ካሕሳይ ብሩ ለአውሎ ሚድያ ተናግረዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ካህሳይ ጨምረውም ጣቢያው የሚያከናውነውን ለውጥ አስተባባሪ ሆነው የተሾሙት አቶ አርአያ ተስፋማሪያም የጣብያዉ ስርጭት ከአዲስ አበባ እንዲሆን ካደረጉ በኋላ ግለሰቡ ባለፈዉ አንድ ወር የግል ስሜታቸዉን በቴሌቭዥኑ አንጸባርቀዉበታል ይላሉ ።

አቶ ካሕሳይ ብሩ አሁንም ቢሆን የጣብያዉ ስራ አስፈጻሚ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ የተሰጠዉ ለኔ ሆኖ እንዳለ ላለፈዉ አንድ ወር ግን ከቁጥጥሬ ዉጭ በሆነ ሁኔታ ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አርአያ ተስፋማርያም በጣብያዉ የሰራተኞት ወርሀዊ ክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ይዘትን በሚመለከት የሚደረገዉ ለዉጥ እንዲያስተባብር የተሰጠዉ ስልጣን በአግባቡ መወጣት አልቻሉም ይላሉ ዋና ስራ አስፈጻሚዉ፡፡

ከዛም ባለፈ ትግራይ ቴሌቭዥን ዋና የስርጭት ጣብያዉ አዲስ አበባ እንዲሆን ጥረት እንዳደረጉ ይሁን እንጂ በጊዚያዊ አስተዳደሩ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አብርሀም በላይ ጥረት የጣብያዉ ዋና ስርጭት በነበረበት በመቐለ ከተማ እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል፡፡

አቶ ካህሳይ በአዲስ አበባ ያለዉ ቅርንጫፍ የጣብያዉ ጽህፈት ቤት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለሚድያችን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት የትግራይ ቴሌቭዥን ከመቐለ በአዲስ ይዘት ስራዉን ለመጀመር ዝግጅቱ ጨርሷል ፤ በቅርብም ወደ ተመልካቾቹ ፕሮግራሙን ማቅረብ ይጀምራ ሲሉ ነው የተናገሩት።

አቶ አርአያ ተስፋማርያም ላለፈዉ አንድ ወር ለተመልካቾች የማይመጥኑ ፕሮግራሞች በቴሌቭዥን ጣብያዉ እንዲተላለፍ አድርገዋል በዚህ ወቅት በትግራይ ቴሌቭዥን ምንም ሚና የላቸዉምበማለት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ታዲያየ ትግራይ ቴሌቭዥን ዋና መስሪያቤት ወደነበረበት መቐለ መዛወሩንም ነግረውናል።

አውሎ ሚዲያ ይህንን በሚመለከት አስተያየታቸዉን ለመቀበል አቶ አርአያ ተስፋማርያምን ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም፡፡

አውሎ ሚድያ ግንቦት 20 / 2013 ዓ.ም