29 ግንቦት 2021, 08:04 EAT

እነሆ ዓመት ተኩል!
ኮቪድ ዓለምን ካመሰቃቀለ ዓመት ከመንፈቅ ነው።
ጊዜው እንዴት ይነጉዳል?
በሰውና በተህዋሲው መካከል ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል። ኮቪድ-19 እየረታም እየተረታም ይገኛል።
እስከ አሁን በጦርነቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሙት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ ቁስለኛ አድርጓል።
አንድ በዓይን የማይታይ ተህዋሲ፣ ከሰማይ ይዝነብ ከምድር ይፍለቅ የማይታወቅ፣ እዚህ ግባ የማይባል ደቃቃ ተህዋሲ የሰው ልጆችን እንዲህ ልክ ያስገባል ያለ ማን ነበር?
የሆነስ ሆነና፣ ተህዋሲው ከየት መጣ? ይህ ቁልፍ ጥያቄ እስከዛሬም እየተጠየቀ ነው። እስከዛሬም እየተመለሰ ነው። ነገር ግን አልተቋጨም።
ምናልባትም አይቋጭም።
ተህዋሲው ቢረታ እንኳ ወደፊት የሚጻፍለት የሕይወት ታሪክ በዚህ ዐረፍተ ነገር ሊጀምር ይችላል።
“ኮቪድ-19 በቻይና አገር፣ በሁቤይ አውራጃ፣ በዉሃን ከተማ ተወለደ…። ዕድሜው የሰውን ልጅ ለመጨረስ እንደደረሰ…።”
በእርግጥ በዉሃን ከተማ ተወልዷል።
ግን የት ቤት ውስጥ ተወለደ? እንደሚባለው ‘ሁውናን’ በሚባለው የባሕር እንሰሳት ጉሊት [ዓሣ ተራ] ነው የተወለደው? ማንስ አዋለደው?
ከሰሞኑ አዲስ መላ ምት ጠንክሯል።
ከዓሣ ተራ ሳይሆን ከቤተ ሙከራ ነው ኮቪድ-19 ያፈተለከው የሚለው መላ ምት ድጋሚ እያነጋገረ ነው።
ይህ መላምት እንዴት የባይደንን ትኩረት ዘግይቶ ሊስብ ቻለ? የዚህ ጽሑፍ ነገረ-ብልት ይኸው ነው።
መላ ምቱ ምን ይላል?
የኮቪድ-19 ተህዋሲ በድንገት ከቻይና የቫይረሶች ጥናት ተቋም አፈትልኳል ይላል መላምቱ።
ለምን ሲባል፣ ምናልባት ቻይና ሆን ብላ ዓለምን ለመቆጣጠር ያደረገችው ይሆን?
ምናልባት የባዮሎጂካል መሣሪያ ፈጥራ ምድርን ልታሸብር አቅሙ እንዳላት ማሳያ ይሆን?
ምናልባት ምዕራቡ ዓለም ምን ያህል ሰው ሠራሽ ተህዋሲዎችን ሊመክት ይችላል የሚለውን ልትለካበት ይሆን?
እነዚህ መላ ምቶች ስሜት ይሰጣሉ? ለአንዳንዶች አዎ!
ለምሳሌ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ባላት ሁሉን አቀፍ ባላንጣነት አዲሱ የውጊያ ግንባር በባዮሎጂካል ሳይንስ ልትከፍት አስባ ሊሆን ይችላል።
በቤተ ሙከራ ተህዋሲዎች የሚመረቱትም ለዚሁ ተግባር ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛው የመላምቱ ማጠናከሪያ በቻይና ሁቤት አውራጃ፣ ዉሃን ከተማ የባሕር እንሰሳት ገበያ አካባቢ የቫይረሶች ምርምር ቤተ ሙከራ መኖሩ ነው።
ይህ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል? ምናልባት!
ሦስተኛው የመላምቱ ማጠናከሪያ ቻይና የተህዋሲው ምንጭ ሆና ተህዋሲውን የተቆጣጠረችበት ፍጥነት የሚታመን ባለመሆኑ ነው።
የተቀረው ዓለም ሥርጭቱን ለመቆጣጠር አሁንም እየተንደፋደፈ ነው። ቻይና ግን ገና ሳይቃጠል በቅጠል ብላ ነው ጸጥ ያሰኘችው።
ቻይና ያላት፣ ሌላው የሌለው ጥበብ ምንድነው? ምናልባት አምጣ የወለደችውን ተህዋሲ ባሕሪ አሳምራ በማወቋ ይሆን?
ሌሎች ደግሞ ቻይና ተህዋሲውን ሆን ብላ አሠራጭታው ላይሆን ይችላል ይላሉ።
ሆኖም በቤተ ሙከራ ተመርቶ በአጋጣሚ አፈትልኮ በቅርብ ኪሎ ሜትር የሚገኘውን የባሕር ምግቦች ጉሊት በክሎስ ቢሆን?
- ባይደን የኮሮናቫይረስ መነሻ በአግባቡ እንዲመረመር አዘዙ
- አሜሪካና ቻይና በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ላይ እየተወዛገቡ ነው
- የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ስላገኘችው ሴት ያውቃሉ?
- ኮሮናቫይረስ ሳይታወቅ ለዓመታት በሌሊት ወፎች ውስጥ ነበር
ሌሎች ግግሞ ተህዋሲው በቤተ ሙከራ ምሕንድስና የተዋለደ ሳይሆን ለምርምር ከባሕር እንሰሳት ወደ ቤተ ሙከራ ተወስዶ ከዚያ አፈትልኮ የወጣ ነው ይላሉ።
እነዚህ መላምቶች ተህዋሲው ዓለምን ማሸበር በጀመረ ሰሞን እየተናፈሱ መጥተው በኋላ ላይ ዶናልድ ትራምፕ እያጠናከሯቸው የመጡ ግምቶች ናቸው።
ኃያላን ወደፊት እግረኛ ጦር የሚልኩበት ጦርነት ላይኖር ይችላል። ኃያላን 3ኛውን የዓለም ጦርነት ከጀመሩ ውጊያው የሚሆነው ወይ በኮምፒውተር ቫይረስ ነው ወይ ደግሞ በባዮሎጂካል ቫይረስ ነው።
ይህ መላምት ሲጠናከር አገራት በቤተ ሙከራ ውስጥ ተደብቀው የሚቀጥለውን እጅግ ከባዱን የጦር መሣሪያቸውን እየፈበረኩ ይሆናል የሚል ነው።
የዚህ ድብብቆሽ የጦር መሣሪያ ውድድር አንዱ መገለጫ ደግሞ ይህ አፈተለከ የተባለው ተህዋሲ ቢሆንስ?
ከዚህ ወዲያ የሚታጠቁት ቦምብ፣ የሚሸከሙት ምንሽር መቼስ አይኖር። የመሣሪያዎች ረቂቅነት ልቆ በዓይን ወደማይታይ ተህዋሲ መውረዱ አይቀርም።
ብዙ የሳይንስ አዋቂዎችና የሚዲያ ተንታኞች እንዲህ ያሉ መላምቶችን ከቁብ ባይቆጥሯቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሩ “አይሆንም አይባልም” እየተባለ ነው። ለምን?

የባይደን ጥርጣሬ?
ከሰሞኑ የአሜሪካ ሚዲያ ጉዳዩን ነክሶ ይዞታል።
ይህ ተህዋሲ ከቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነው የሚሉ ሐሳቦች እየተብላሉ ነው።
ይህን ቸል ተብሎ የነበረ መላምት እንደ አዲስ የቀሰቀሱት ደግሞ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ናቸው።
ለሳይንቲስቶቹ መነሻ የሆነው ደግሞ በምስጢር ተይዞ የነበረ አንድ የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሰነድ ነው።
ሰነዱ ምን ይዟል?
በዉሃን ቤተ ሙከራ ውስጥ በኅዳር ወር 2019 አካባቢ ሦስት የቤተ ሙከራው ተመራማሪዎች አመም አድርጓቸው ሆስፒታል ሲታከሙ ነበር።
ይህ የጊዜ ስሌት ወዴት ይወስደናል?
ጊዜውን ተህዋሲው ከባሕር እንሰሳት ጉሊት ተነሳ ከተባለለት ጊዜ ጋር ስናገጣጥመው ተመራማሪዎቹ ታመው የታከሙት ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ እንደሆነ እንረዳለን።
ይህም መረጃ ነው ሳይንቲስቶቹን ምናልባት ተህዋሲው ከጉሊት ሳይሆን ከቤተ ሙከራ የወጣ ነው እንዲሉ ያስቻላቸው።
ይህን መላምት ተመሥርቶም ትራምፕ አንድ ምርመራ እንዲጀመር አዘው ነበር፣ ያኔ። ባይደን ሲመጡ ምርመራው ቆመ።
ዝነኛው የተላላፊ በሽታዎች ሐኪምና አሁን የጆ ባይደን የጤና ጉዳዮች ልዩ አማካሪ ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ ለሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደራሴዎች ሲናገሩ “ይህ መላምት ውሃ የማይቋጥር የሚባል አይደለም፤ ምርመራው መቀጠል አለበት” ብለው ነበር።
የእሳቸውን ንግግር ተከትሎ ምርመራው ቢቀጥልም ውጤቱ እስከዛሬ ይፋ ሳይደረግ ቆይቷል።
ባይደን አሁን የዚህ ምርመራ ውጤት በአስቸኳይ ይቅረብልኝ፣ ምርመራውም ተጠናክሮ ይቀጥል እያሉ ነው።
በዚህን ጊዜ ዶናልድ ትራምፕ ደስ አላቸው። ለኒውዮርክ ፖስት ጋዜጣም “ነግሪያችሁ ነበር እኮ…” የሚል ደብዳቤ ጻፉ።
“ገና ድሮ ተናግሬ ነበር። እኔ ገና ነገሩ ሲጠነሰስ ጀምሮ አውቄዋለሁ። ሰው ሁሉ ግን ወረደብኝ፤ አብጠለጠለኝ፤ አሁን ሁሉም ሰው ‘ለካንስ ትራምፕ እውነቱን ነበር’ እያለኝ ነው” ሲሉ ማስታወሻ ቢጤ ለጋዜጣው ከትበዋል።

ሳይንቲስቶች ምን አሉ?
ሳይንቲስቶች ብዙ እያሉ ነው። ነገሩ በእነርሱ መካከልም ትልቅ መነጋገርያ ሆኗል።
የዓለም ጤና ድርጅት ምርመራ ነገሩን ሁሉ ያጠራዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ የላከው ቡድን ከብዙ መልስ ይልቅ ብዙ ጥያቄ ይዞ ነው የተመለሰው።
ቡድኑ 12 ቀናትን በዉሃን ከተማ ካሳለፈ በኋላ “ከቤተ ሙከራ ተህዋሲው አፈተለከ ለማለት የሚያስችል ጠንካራ ነገር አላገኘሁም” ብሏል።
ነገር ግን ብዙዎች የቡድኑን አጠራጣሪ ድምዳሜ ተጠራጥረውታል።
ቡድኑ ኮቪድ-19 ከቤተ ሙከራ አምልጦ ይሆናል የሚለውን መላምት በቁም ነገር ወስዶ ምርመራ አላደረገም እየተባለ ይተቻል።
ራሳቸው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ሳይቀሩ ሁሉም መላምቶች ለምርመራ ክፍት መሆን አለባቸው፤ አዲስ ምርመራ ሊጀመር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር ፋውቺ አሁን እያሉ ያሉት ተህዋሲው በተፈጥሮ የመጣ ነው የሚለውን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ነው።
ዶ/ር ፋውቺ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከዚህ በተቃራኒው ነበር የሚያስቡት። አሁን ሐሳባቸውን ምን እንዳይስቀየራቸው እንጃ።
ምናልባት ለሕዝብ ይፋ ያልተደረገ ሰነድ ከደኅንነት ቢሮ አግኝተው ይሆን?
ቻይና ምን አለች?
ቻይና ከሰሞኑ ይህን ተህዋሲ በቤተ ሙከራ አምርተሻል መባሏ አስቆጥቷታል። አብግኗታል። የቃል አጸፋ መመለስ ይዛለች።
ይህ እኮ የምዕራባዊያን የተለመደ ስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ብላለች።
በነገራችሁ ላይ፣ ቻይና ተህዋሲውን በቤተ ሙከራ ሠራሽው የሚለውን ክስ ብቻ ሳይሆን ተህዋሲው ከአገሯ እንደተነሳም አታምንም።
ምናልባት የባሕር ምግቦች በማቀዝቀዣ በኮንቴይነር ከእሲያ አገሮች ወደ ቻይና ሲጓጓዙ አብሮ የገባ ተህዋሲ ይሆናል ነው የምትለው።
የተህዋሲው መነሻም የደቡብ ምዕራብ እሲያ አገራት ሊሆኑ ይችላሉ ነው የምትለው።
የቻይና ቁልፍ የሥነ ተህዋሲያን ሊቅ የሆነችው ፕሮፌሰር ሺ ዘንግሊ [በቅጽል ስሟ የቻይናዋ ባትዎማን ይሏታል] ባለፈው ሳምንት አዲስ ግኝት አሳትማለች።
ይህቺ ታላቅ ቻይናዊት ሳይንቲስት በዉሃን ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ናት።
የምርመራ ውጤቷ እንዳመላከተው የተህዋሲው ‘መልክና ቁመና’ ከሩቅ አካባቢ የማዕድናት ማውጫ ሰፈር ከመጣ የሌሊት ወፍ ላይ ከተገኘ ተህዋሲ ናሙና ጋር ምስስሎሽ አለው።
ሌላ መላምት አለ?
አዎን አለ።
በዚህ ገለልተኛ ጎራ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ተህዋሲው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከእንሰሳት ወደ ሰው የተላለፈ ነው ብለው ያምናሉ።
ኮቪድ-19 ከሌሊት ወፍ ነው የመጣው። የሌሊት ወፍ ምናልባት ለሌላ እንሰሳ አስተላለፈችው፤ ሌላኛው እንሰሳ በውክልና ራሱ ጋር አቆይቶት ሲያበቃ ወደ ሰው አዛመተው ብለው ይገምታሉ።
ይህ መላምት ተህዋሲው መዛመት በጀመረ ሰሞን በስፋት ይታመን የነበረና በጊዜ ሂደት ግን እየተሸረሸረ የመጣ ነው።
ከየትስ ቢመጣ እኛ ምናገባን?
ይህ ተህዋሲ በዓለም ላይ 3 ሚሊዮን ተኩል ሕዝብ ጭጭ አድርጓል።
ምናገባን የሚባል ሊሆን አይችልም።
በቀጣይ ሌላ የሰው ልጆችን እልቂት እንደዋዛ የሚያመጣ ተህዋሲ ሊኖር ይችላል።
ያ ከመምጣቱ በፊት የሰው ልጅ ስለዚህ ተህዋሲ ድብን፣ ጥርት አድርጎ ሊያጠና ይገባዋል።
የሰው ልጅ እንደሚታሰበው በጣም አልተራቀቀም። ወይም በጣም ተራቋል። መቆያውንም መጥፊያውንም በማምረት የተጠመደ የሰው ዘር ተራቋል ነው የሚባለው?
ተህዋሰው እንደሚባለው ቻይና በቤተ ሙከራ አምጣ-ወልዳው ከሆነ ደግሞ አጥፊያችንም አዳኛችንም ወይ ቻይና፣ ወይ ባላንጣዎቿ ኃያላን ናቸው።