30 ግንቦት 2021, 08:49 EAT

በካናዳ 215 ህፃናት የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ተገኝቷል።
ስፍራው የቀድሞ ትምህርት ቤት ሲሆን የካናዳ ቀደምት ህዝቦችን ወደ ነጭ ባህል ለማላመድ በሚል የተመሰረተ ነው።
ካምሎፕስ ኢንዲያን ሬዚደንሻል ትምህርት ቤት የሚል መጠሪያ በተሰጠው ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ ህፃናት ናቸው አፅማቸው የተገኘው።
ትምህርት ቤቱ በአውሮፓውያኑ 1978 ተዘግቷል።
የህፃናቱ በጅምላ መቀበር ያሳወቁት የቴኬኤምሉስፕ ቴ ሴክዌፑምክ ቀደምት ህዝቦች መሪ በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ነው። ከነዚህ ተማሪዎች መካከል እስከ ሶስት አመት ድረስ ህፃናት እንደነበሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጠቁሟል።
- በትግራይ የዘር ጭፍጨፋ ክሶችና የረሃብ ስጋት
- የአሜሪካ ማዕቀብ በቀጣናው ስትራቴጂያዊ ለውጥን ያስከትል ይሆን?
- በሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት ከወራት በኋላ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንደሚጀምር አስታወቀ
እነዚህ ትምህርት ቤቶች የቀደምት ህዝቦች ልጆች በአዳሪነት የሚማሩባቸው ናቸው።
ከአውሮፖውያኑ 1863-1998 150 ሺህ የሚሆኑት እነዚህ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ተወስደው በነዚህ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ነበር።
በራሳቸው ቋንቋ መናገርም ሆነ ባህላቸውን እንዲከተሉ አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ከፍተኛ ጥቃቶችንም አስተናግደዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስትን ትሩዶ “በአገራችን ታሪክ ውስጥ አሳፋሪ የሚባለውን በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያስታውሰን ነው” ብለዋል።
የካናዳ ቀደምት ህዘቦች ከሙዝየምና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ህፃናቱ የሞቱበት ወቅት እንዲሁም ምክንያት ለማወቅ እየሰሩ ነው። ህፃናቱ እንዴት ሞቱ ለሚለው እስካሁን እርግጥ የሆነ ምላሽ አልተገኘም።
ካምፕሉስፕ የተሰኝችው ከተማ የማህበረሰብ መሪ ሮዛኔ ካስሚር እንዳሉት የህፃናቱ ሞት በትምህርት ቤቱ አስተዳደር እንዳልተመዘገበና የማይታሰብ ጥፋት እንደተፈፀመ ማሳያ ነው ብለዋል።
ካምሉፕስ ኢንዲያን ሬዚደንሻል ስኩል የነጮችን ባህል ለማላመድ ከተከፈቱ ትምህርት ቤቶች መካከል ትልቁ ነው።
በሮማን ካቶሊክ አስተዳደር የበላይነትም ሲሆን የተከፈተው ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1890 ነው። የተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው በተባለበት በአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግድ ነበር።
ማዕከላዊው መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1969 የማስተዳደሩን ሁኔታ ከተቀበለ በኋላ ለአካባቢው ተማሪዎች እንደ አዳሪ ትምህርት ቤት ይገለገሉበት የነበረ ሲሆን በ1978ም ተዘግቷል።