May 31, 2021


May be an image of one or more people, people sitting and indoor

(አሚኮ) በኩባ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡሩኒ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ጋር ተወያይተዋል።

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ዋና ዳይሬክተርነት የአፍሪካ ሕብረት ዶክተር አርከበ እቁባይን በእጩነት ማቅረቡን በተመለከተ እና በቀጣናዊና የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ነው ውይይት ያደረጉት።

አምባሳደሩ ሽብሩ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ላላት ግንኙነት የላቀ ግምት እንደምትሰጥ እና የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ-ብዙ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዶክተር አርክበ እቁባይ ለተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ጄኔራል ዳይሬክተርነት የመጨረሻ ሦስት ዕጩዎች ውስጥ መካተታቸውን በአፍሪካ ሕብረት በኩል ሙሉ ድጋፍ የተሰጣቸውን የአፍሪካ ብቸኛ ተወዳዳሪ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ዶክተር አርከበ ካላቸው አቅም እና ድርጅቱን ለመምራት ካስቀመጡት ራዕይ አንጻር ቢመረጡ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት እንደሚሠሩ ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያሉትን ልዩነቶች በውይይትና በድርድር ለመፍታትና ሁሉንም ወገን በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ ስምምነት እንዲደርስ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ገልጸዋል። ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ መፍሔሄ የሚገኝበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ኢትዮጵያ እየሠራች መሆኑን አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ሽብሩ ለኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ፣ በቅርቡ ስለሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና መንግሥት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የሕግ ማስከበር ርምጃ በተመለከተ ለክቡር ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡሩኒ ሮድሪጌዝ ፓሪላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሚመራው መንግሥት የሚያካሂደውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም እንደሚደግፉ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ያቀረበቻቸውን እጩ ኩባ በአዎንታዊ መልኩ ወስዳ እንደምታየው ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ለመፍታት እያደረገችው ያለው ተግባር ኩባ እንደምትደግፈውና እውቅና እንደምትሰጠው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን እና ኩባ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ለማሳደግ ሀገራቸው እንደምትፈልግም መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡