የቻይና ኤምባሲ በኦነግ ሸኔ ታግተው የነበሩ ዜጎቹን ከቀይ መስቀል ተረከበ

May 31, 2021


ዓለም አቀፉ የቀይ መስል ማኅበር በምዕራን ኦሮሚያ ውስጥ ከሳምንታት በፊት ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን መቀበሉን አረጋገጠ።

የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ እንደገለጹት ቀይ መስቀል ሦስቱን የቻይና ዜጎች ይዟቸው ከነበረው ታጣቂ ቡድን ተቀብለው ለአገራቸው ኤምባሲ አሳልፈው ሰጥተዋል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራውና መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለውና በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ቡድን ነው ብሎ የሰየመው ታጣቂ ቡድን፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቻይናውያኑን በቁጥጥሩ ስር እንዳስገባ አሳውቆ ነበር።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ አዲስ አበባ ያለው የቻይና ኤምባሲ ስለግለሰቦቹ በታጣቂው ቡድን እጅ መግባት በተመለከተ ያሉት ነገር አልነበረም።

ከሳምንታት በኋላ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ቡድኑ ቻይናውያኑን መልቀቁንና ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ማስረከቡን የሚገልጽ በሰነድና በፎቶግራፍ የተደገፈ መግለጫ አውጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ ቢቢሲ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ባደረገው ማጣራት በታጣቂው ቡድን ታግተው የነበሩት ሦስት ቻይናውያን ማዕድን አውጪ ሠራተኞች መቀበሉን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአገራቸው ኤምባሲ ተላልፈው እንደተሰጡ የማኅበሩ ሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰር አልዮና አስታውቀዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ታጣቂ ቡድኑ ቻይናውያኑን ስለማገቱ ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ አቅራቢያ “በመንግሥት እና በማዕድን አውጪዎቹ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ሕጋዊ አይደለም” በሚል ምክንያት ሠራተኞችን “አግቼ ይዣለሁ” ብሎ ነበር።

ቡድኑ በምዕራብ ኦሮሚያ መነ ሲቡ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ ውስጥ ያዝኳቸው ያላቸውን ሦስት የቻይና ዜግነት ያላቸውን ሰዎች መያዙን ከግለሰቦቹ ፎቶግራፍ ጋር አያይዞ ባወጣው መግለጫ አሳውቆ ነበር።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር (አይሲአርሲ) ሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ ማኅበሩ ሦስቱን ቻይናውያንን ተቀብሎ ለቻይና ኤምባሲ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ “ማኅበሩ በኃላፊነቱ መሠረት ገለልተኛ ሆኖ ሦስቱ ቻይናውያን ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ለቻይና ኤምባሲ ተላልፈው እንዲሰጡ አስተባብሯል” ብለዋል።

የሕዝብ ግነኙነት ኦፊሰሯ አይሲአርሲ በጉዳዩ ላይ የነበረው ኃላፊነት ፍጹም ሰብዓዊነት ላይ የተመሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ታግተው የነበሩት ቻይናውያን በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ በለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

Image