1 ሰኔ 2021, 08:23 EAT

የዓለም ጤና ድርጅት አርማ

የዓለም ጤና ድርጅት ለአዳዲሶቹ የኮቪድ-19 ዝርያዎች ስም ለመስጠት የሚያስችል ስርአት ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

ከዚህ በኋላም ድርጅቱ የቫይረሱን አይነቶች ለመለየት የግሪክ ፊደላትን የሚጠቀም ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ አፍሪካና ሕንድ ውስጥ የታዩት አዳዲስ ዝርያዎች መጀመሪያ ስያሜ ይሰጣቸዋል።

ለምሳሌም በዩናይትድ ኪንግደም የታየው አዲሱ ቫይረስ ዝርያ ‘አልፋ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። የደቡቡ አፍሪካው ‘ቤታ’ የተባለ ሲሆን በሕንድ በርካቶችን ያጠቃው የቫይረስ አይነት ደግሞ ‘ዴልታ’ ተብሎ እንደሚጠራ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ስያሜዎቹን ያስተዋወቅኩት አንደኛ በንግግር ወቅት ቀላል ለማድረግና በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቫይረሱ ዙሪያ የሚኖሩ የተለያዩ ማግለሎችን ለማስቀረት ነው ብሏል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ወር መጀመሪያ አካባቢ የሕንድ መንግሥት በአገሪቱ የተገኘውን የኮቪድ-19 አዲስ ቫይረስ ‘ቢ.1.617.2’ የሚል ስያሜ መስጠቱን ተከትሎ በርካታ ትችቶችን አስተናግዶ ነበር።

”የትኛውም አገር አዲስ የቫይረሱ አይነቶችን ሪፖርት በማድረጉ መገለል ሊደርስበት አይገባም” ብለዋል የዓለም ጤና ደርጅት ቴክኒካል መሪ የሆኑት ማሪያ ቫን ኬርኮቭ።

አክለውም አገራት አዲሶቹ ቫይረሶች ላይ ጠበቅ ያለ የክትትልና የምርመራ ስራ እንዲያከናውኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አዲሱ የቫይረሶቹ ስያሜ ከተለያዩ ነገሮች አንጻር ከግምት ውስጥ እንደገባ የተገለጸ ሲሆን የሁሉም ቫይረሶች ስም ዝርዝር በዓለም ጤና ድርጅት ድረገጽ ላይ ይፋ ተደርጓል።

እነኚህ የግሪክ ፊደላት አሁን በጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙትን ሳይንሳዊ ስሞች የሚተኩ አይደለም።

አዲሶቹ የኮሮናቫይረስ አይነቶች ከ24 የሚበልጡ ከሆነ የተዘጋጀው ስርአት ፊደላት ያልቁበታል። በዚህም መሰረት አዲስ ስያሜ የመስጠት ስርአት ይዘረጋል ብለዋል ማሪያ ቫን ኬርኮቭ።

”እኛ እያልን ያለነው እንደ ቢ.1.617.2 ያሉ ሳይንሳዊ ስያሜዎችን ሙሉ በሙሉ መቀየር ሳይሆን ሁሉም ሰው የሚረዳው አይነት ስያሜ እንስጠው ነው። ስያሜው ቀለል ሲል ማህበረሰቡ በዕለት ተዕለት ግንኙነቱ ይጠቀማቸዋል” ብለዋል።

ሰኞ ዕለት የዩናይትድ ኪንግደም መንግስትን የሚያማክሩ ተመራማሪዎች አገሪቱ በሶስተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። በዋነኛነት ሰዎችን እያጠቃ የሚገኘውም ‘ዴልታ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው የሕንዱ ዝርያ ነው።

ይህ ዝርያ ‘አልፋ’ የሚል ስያሜ ከተሰጠው የዩኬው ዝርያ በበለጠ መልኩ በቶሎ መሰራጨት የሚችል ሲሆን በዩኬ ለጨመረው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምክንያት ነው።

በሌላ በኩል በቬትናም የተስተዋለው አዲሱ የቫይረስ አይነት በሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከታዩት የቫይረሱ ዝርያዎች የተቀላቀለ ሲሆን በቀላሉ በአየር መተላለፍ የሚችል ነው።