የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፈሪ ፌልትማን በአራት አገራት የሚያደጉትን ጉብኝት መጀመራቸውን የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።

ፌልትማን ካለፈው ሰኞ ግንቦት 23 ጀምሮ እስከ መጪው ቅዳሜ ግንቦት 29 ድረስ በሚያደርጉት ጉዞ ኳታርን፣ ሳዑዲ አረቢያን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን እና ኬንያን ይጎበኛሉ።

የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ፌልትማን በዚህ ጉዟቸው በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስላሉ ጉዳዮችና እና በአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ይወያያሉ ተብሏል።

የልዩ መልዕክተኛውን ጉዞ በተመለከተ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ፌልትማን ከየአገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ።

የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው፤ ልዩ መልዕክተኛ ፌልትማን ከአራቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እና የበለጸገ እንዲሆን መደገፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራሉብሏል።

ጨምሮም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት በሁሉም አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስምምነት እንዲደረስእንደሚመክሩ መግለጫው አትቷል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው መግለጫ ያወጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ ልዩ መልዕክተኛቸው በዚህ ሳምንት ወደ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ተመልሰው እንደሚያቀኑ የገለጹ ቢሆንም፤ በዚህ ዙር ጉዟቸው ግን ዋነኛ ትኩረታቸው የመካከለኛውና የባሕረ ሰላጤው አገራት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።

line

ልዩ መልዕከተኛው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ኬንያ ለምን?

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ የሚጎበኟቸው አገራት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ውስጥ እየጎላ የመጣ ሚና ያላቸው ሲሆን አሜሪካ ጥረቷን እንዲያግዙ ከጎኖ እንዲሰለፉ ለማድረግ እንደሆነ ይገመታል።

ኬንያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምሥራቅ አፍሪካ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እየጎላ መጥቷል። የጆ ባይደን አስተዳደር የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በቅርቡ ከኬንያ ጋር የጦር ልምምድ ለማድረግ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ጦር ወደ ኬንያ እንደሚልክ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

በባሕረ ሠላጤው ብሎም ከዚያ ባሻገር ተጽእኖዋ እየጎላ የመጣው ኳታር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት የደኅንነትና የዲፕሎማሲ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

ቀደም ሲል ከሱዳንና ከኤርትራ ጋር የቀረበ ግንኙነትን ያዳበረችው ኳታር ከቀርብ ዓመታት ወዲህ ከኢትዮጵያና ከሶማሊያ ጋርም ግንኙነቷን አጠናክራላች። በዚህም በሱዳንንና በኤርትራ እንዲሁም በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረት ማድረጓ ይታወሳል።

ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመካከለኛው ምሥራቅና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ሰፊ ተጽእኖ ያላቸው አገራት ሲሆኑ በአፍሪካ ቀንድም የማይናቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።

ሁለቱ አገራት ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኤርትራና ኢትዮጵያ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ጠላትነታቸውን እንዲያበቁ በማድረግ በኩል የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታመናል። በተጨማሪም በኢኮኖሚና በደኅንነት በኩል ያላቸው ግንኙነት ቀላል የሚባል አይደለም።

line

የፌልትማን የከዚህ ቀደሙ ጉብኝት

ከጥቂት ወራት በፊት በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ፌልትማን ከሳምንታት በፊት ግብጽን ጨምሮ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጉዞ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ፌልትማን በመጀመሪያው ጉዟቸው ከሚያዚያ 26 እስከ ግንቦት 5 2013 .ም ባሉት ቀናት ወደ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ተጉዘው ነበር።

በዚህም በትግራይ ያለው ግጭት እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓመታት በዘለቀው አለመግባባት ዙሪያ ግፊት ለማድረግ የፈለጉት በአገራቱ ወዳጆች በኩል እንደሆነ የጉዟቸው አቅጣጫ ያመለክታል።

ጉዟቸውን በግብጽ ጀመረው የነበሩት ፌልትማን፤ በካይሮ ቆይታቸው ከግብጽ ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው ነበር።

በውይይታቸው ወቅት አልሲሲ ግብጽ ከአባይ ውሃ የምታገኘው ድርሻ መቀነስን አትታገስም በማለት ስለመናገራቸው ዋሽግተን ፖስት ዘግቦ ነበር።

አምባሳደር ፌልትማን በበኩላቸው የጆ ባይደን አስተዳደር በቀጠናው ላሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት ትኩረት ያደርጋል ሰለማለታቸው ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን ጠቅሶ ጨምሮ ዘግቧል።

ፌልትማን ወደ አሥመራ በተጓዙ ወቅትም ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ረዘም ላለ ሰዓት መወያየታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀው ነበር።

አራት ሰዓት በቆየው ውይይት ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ኤርትራ ከአሜሪካ ጋር አብራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል ሲሉ የማስታወቂያ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

line

ፌልትማን ማን ናቸው?

ጄፍሪ ፌልትማን በሹመታቸው ወቅት በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቆ ነበር።

ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።

ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ዋና ጸሐፊዎች ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሊባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።

ቢቢሲ