ቢልለኔ ስዩም እና ጌዲዮን ጢሞቲዮስ

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተዋል የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በበርካታ ወገኖች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ሲጠየቁ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት መውጣት ጀምረዋልብለዋል።

ሰባት ወራትን ባስቆጠረው የትግራይ ክልል ቀውስ ውስጥ ተፈጽመዋል በተባሉ ጾታዊ ጥቃቶችና ግድያዎችን ጨምሮ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰሱ የቆዩት የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው የገቡት የደኅንነት ስጋት ስለነበራቸውእንደሆነ ተገልጾ ነበር።

በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ የሚወተውቱት የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ከተወያዩ በኋላ ወታደሮቻቸው ከኢትዮጵያ እንደሚወጡ የተገለጸ ቢሆንም አስካሁን ድረስ በይፋ የተገለጸ ነገር አልነበረም።

አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት መውጣት መጀመራቸውን አመልክተዋል።

በትግራይ ስላለው ሁኔታ በተሰጠው መግለጫ ላይ ምን ተባለ?

ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 26/2013 . ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የጽህፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩምና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (/) በትግራይ ክልል ውስጥ ስለተከሰተውና አሁን ስላለው ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም መሠረት በክልሉ ስላለው የጸጥታ ሁኔታ፣ የእርዳታ አቅርቦት፣ ተፈጸሙ ስለተባሉ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በመንግሥት በኩል እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች ሁለቱ ባለሥልጣናት ማበራሪያ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም በመግለጫው መንግሥት አሁን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ ያለው በሁለት አካባቢዎች ብቻ መሆኑን ቢያመለክቱም እነዚህ አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ አልጠቀሱም።

የዕርዳታ አቅርቦት

በትግራይ ክልል በአንድ ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች፣ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር ደግሞ ለ4.3 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋሞች በትግራይ እርዳታ የሚሹ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እንዲሁም ክልሉ የረሃብ አደጋ እንደተጋረጠበትም መግለጻቸው ይታወሳል።

ቃል አቀባዩዋ በበኩላቸው መንግሥት ከእርዳታ ሰጪ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በ93 ወረዳዎች እርዳታ እየተሰጠ ነው ብለዋል። ከእነዚህ መካከል 14 ወረዳዎች በመንግሥት የተቀሩት ደግሞ በረድዔት ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል።

በክልሉ ያለውን ሁኔታ በማስመልከት የተለያዩ አገሮች ያሳዩትን አቋም የኢትዮጵያን ክብር ያልጠበቀሲሉ ገልጸውታል። የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነው ሲል በተደጋጋሚ መውቀሱ አይዘነጋም።

በክልሉ እየተደረገ ባለው ሰብዓዊ እርዳታ በ5.2 ሚሊዮን ብር 166 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ተከፋፍሏል ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ሪሊፍ ሶሳይቲ ኦፍ ትግራይን ጨምሮ 6 የረድዔት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር እርዳታ እያቀረቡ እንደሚገኙም አክለዋል።

ረሃብ እንደ ጦርነት መሣሪያ አየዋለ ነው የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውምሲሉም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾችን ክስ አጣጥለዋል።

የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለው የእርዳታ አቀርቦት በሚፈለገው ሁኔታ እየተከናወነ ባለመሆኑ ቁጥሩ ከፍ ያለ ሕዝብ ለረሃብ ይጋለጣል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በጤና ድጋፍ ረገድ 72.9 ሚሊዮን ብር እንደተመደበና 12 አምቡላንስ መሠማራታቸውን ጠቅሰው የህክምና አገልግሎት መስጫ ሙሉ በሙሉ ወድሟል የሚለው ትክክል አይደለምብለዋል ቢልለኔ።

በሌላ በኩል የግብርና ሚንስትር ዘርና ማዳበሪያ ለማከፋፈል እንዲሁም የክልሉን አርሶ አደር ለመደገፍ 10 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅሰዋል።

ትምህርትን ዳግመኛ ለማስጀመር ደግሞ 95 ሚሊዮን ብር መመደቡን ቢልለኔ ጠቅሰዋል።

የወንጀል ምርመራ

በሌላ በኩል የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌድዮን ጢሞቲዮስ (/) በበኩላቸው በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ በሕግ በኩል እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎችና ተፈጸሙ ከተባሉ የመብት ጥሰቶች አንጻር ስለተደረጉ ምርመራዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ህወሓት በአፋር፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚያስታጥቃቸው እና የሚደግፋቸው ኃይሎች የአገር ሰላም እያናጉ ነውብለዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ በሰሜን ዕዝ ላይ የተቀነባበረ ጥቃት ተፈጽሟልበማለት በተያያዥም የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች በህወሓት አመራር መቋረጣቸውን አስታውሰው ብዙዎቹ በወንጀል የሚጠረጠሩት ታስረዋልብለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግሥትን በመጣስ፣ በሽብርተኛነት እና በሌሎችም ወንጀሎች እንደሚጠየቁ በመግለጫቸው ላይ አመልከክተዋል።

በወሲባዊ ጥቃት፣ ተዋጊ ባልሆኑ ሰዎች ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተም ምርመራ ተደርጎ እርምጃ እተወሰደ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም መሠረት 28 ወታደሮች ክስ እንደተመሠረተባቸው እና በወሲባዊ ጥቃት የተጠረጠሩ 25 ወታደሮችም ላይም ክስ እንደተከፈተ ጌድዮን (/) ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በማይካድራ የ250 የዓይን እማኞች ተጠይቀውና የፎረንሲክ ምርመራ በከተደረገ በኋላ ከ200 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እንዲሁም የወንጀሉ ተሳታፊ የተባሉ 23 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን አመልክተዋል።

በዚሁ ጥቃት ላይ ተሳትፈዋል የሚባሉ ብዙዎቹ ግን ወደ ሱዳን ሸሽተዋልሲሉም አክለዋል።

የአክሱም ግድያን በተመለከተ፤ ከ100 የዓይን እማኞች እና የህክምና ማስረጃ በተገኘ መረጃ መሠረት “100 ንጹሃን መሞታቸውን ደርሰንበታል። አብዛኞቹ ህወሓት ያስታጠቃቸው፣ ሁለት ቀን የሰለጠኑ ኢመደበኛ ተዋጊ ናቸውብለዋል ዐቃቤ ሕጉ።

በአክሱም ከተገደሉት መካከል 40 የሚሆኑት ውጊያ ውስጥ ያልነበሩ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ምርመራቸው ንጹሃን እንደተገደሉና መሠረተ ልማት ላይም ጉዳት እንደደረሰ እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ንጹሀን ላይ ደርሰዋል በተባሉት ጥቃቶች የኤርትራ ወታደሮች እጅ አለበት? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በአንዳንዶቹ ወንጀሎች አሉበትሲሉ ጌድዮን (/) ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መቼ እንደሚወጡ የተጠየቁት ቢልለኔ፤ ጥያቄው ለሚመለከተው አካል እንደቀረበ ገልጸው በመከላከያ ሚንስትር ሪፖርት መሠረት ሂደቱ ተጀምሯልብለዋል።

ቢቢሲ