
እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር
እውቀት ተሸክሞ መጣልህ መምህር
–
… ዛሬ ደግሞ ሌላ በሚጣፍጡ የእውቀት ፍሬዎች የተመላው ግዙፍ ዋርካ መውደቁ ተሰምቷል። አይደለም ተንቀሳቃሽ ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት ነው የወደመው የሚሉም አሉ። ባለማዕተቡ አረጋዊው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም የእነ የኔታ ጥበቡን፣ የእነ የኔታ አክሊሉን መንገድ ተከትለው ዛሬ ወደፈጠራቸው መጠራታቸውን ሰማን። ነፍስ ይማር !!
–
አንጋፋው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።ፕሮፌሰር ጌታቸው ከ1950 አስከ 1960ዎቹ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ በሴማዊ ቋንቋ ጥናት፣ በአማርኛ ግዕዝ ሥነ-ጹሑፍ እና ሰዋሰው በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
–
በአማርኛ ቋንቋ ከታተሙ ሥራዎቻቸው መካከል ደቂቀ አስጢፋኖስ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ ስለግዕዝ ሥነ-ጹሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች፣ ባሕረ ሐሳብ የሚሉት ይገኙበታል።ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሀገራዊ ጉዳዮች በሚሰጡትም በሳል ሀሳቦች እና ትችቶችም በሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ።
–
… አዋቂዎች… ተጠያቂ ሊቃውንት… አስታራቂ ሽማግሌዎች… የታሪክ ምስክሮች የሆኑ አራት ዐይና ኢትዮጵያውያን ምሑራን በሙሉ በእሽቅድምድም በሚገርም ፍጥነት እየተለዩን ነው። በምድሪቱም ላይ ዝግባ ዝግባው እየወደቀ እንቦጭ እንቦጩ እያበበ፣ እየደመቀ ነው። ለራስ ማልቀስስ አሁን ይህን ጊዜ ነው።
… ከምር እየደነቀኝ ነው። ከቤተ መቅደሱም… ከሃገር ከመንደሩም… አስታራቂ ሽማግሌም ተጠያቂ ሊቃውንቱም በፍጥነት እየተለዩን ነው።
–
በሰላም ይረፉ ፕሮፌሰር !!ዘመድኩን