ከ 2 ሰአት በፊት

አንዲት ሐኪም ክትባት ይዛ
የምስሉ መግለጫ, በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ክትባት ኣስፈልጋል

አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ በሚስፋፋ በሦስተኛ ደረጃ የኮሮረቫይረስ ወረርሽኝ ማዕበል ውስጥ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ይህንንም ለመግታት ተጨማሪ ክትባተ በአፍሪካ አገራት ውስጥ መሰራጨት እንዳለበት ድርጅቱ አሳስቧል።

አስካሁን በአፍሪካ አገራት ውስጥ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች አሃዝ ከአምስት ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን፤ ቢያንስ ሰባት አገራት ለሕዝባቸው የሚያቀርቡት ክትባት አልቆበቀቸዋል።

“አፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን አሁን በአስቸኳይ ማግኘት ያስፈልጋታል” ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኃላፊ ዶክተር ማሲሂዲሶ ሞኤቴ ናቸው።

ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ቱኒዚያ፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በአህጉሪቱ ውስጥ ከፍተኛውን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ያስመዘገቡ አገራት ናቸው።

ኡጋንዳና ናሚቢያ ደግሞ እጅግ አስከፊ በሆነው ሦስተኛው ዙር የወረርሽኙ ማዕበል ውስጥ ሲሆኑ በርካታ ሰዎች በየቀኑ እየሞቱባቸው መሆኑም ተገልጿል።

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በአጠቃላይ 136,030 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ለህልፈት መዳረጋቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በአፍሪካ የተለያዩ አይነት የኮሮናይረስ ዝርያዎች እንደተገኙ የገለጸው የዓለም ጤና ድርጅት ‘ዴልታ’ የተባለው ዝርያ በ14 አገራት ውስጥ የተገኘ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መኖሩ የታወቀው ‘ቤታ’ የተባለው ዝርያ ደግሞ በ25 አገራት ውስጥ ተስፋፍቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው አስካሁን ተጨማሪ ክትባቶች ለአፍሪካ አገራት መቼ እንደሚቀርብ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ በአህጉሪቱ ውስጥ በጣም አጣዳፊ የክትባት ፍላጎት አለ ብሏል።

በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ዓይነት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ተሰራጭተው አገልግሎት ላይ እየዋሉ ሲሆን የአፍሪካ አገራት ከሚያስፈልጋቸው በታች መጠን ያለው ክትባት አግኝተው ሕዝባቸው እየተከተቡ ነው።

አስካሁን በአህጉሪቱ ካለው ሕዝብ ሁለት በመቶው ያህሉ ብቻ ክትባቱን ያገኘ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ይህ ግን ከሚጠበቀው በታች ነው ተብሏል።